ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን ለማስፋፋት የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ትፈልጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን ለማስፋፋት የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ትፈልጋለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን ለማስፋፋት የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንደምትሻ የከተማና መሰረተልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የከተማና መሰረተልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በዱባይ እየተካሄድ በሚገኘው የኮፕ-28 ጉባኤ አካል በሆነው የፓናል ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማትን በማፋጠን ያላትን ልምድ አቅርበዋል።
የፓናል ውይይቱ ዱባይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ውስጥ ነው የተካሄደው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ነመራ ገበየሁ(ዶ/ር)ና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ስራ አስፈጻሚ መለከት ሳህሉ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማት እንዲፋጠን የግሉን ዘርፍ ሚናን ለፓናሉ ተሳታፊዎች አቅርበዋል።
የከተማና መሰረተልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በወቅቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ የአየረን ንበረት እርምጃዎችን ከሀገራዊ ልማቱና ከግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ጋር በማጣጣም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የከተማ ልማትን እውን ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣በመረጃ የዳበረና ዘላቂ የሆነ የከተማ ፕላን ያስፈልጋል።
“የታዳሽ ሃይልን በማጠናከር፣ስማርት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ፣የሀይል አጠቃቀምን በማመጣጠንና ስነ ምህዳራችንን በመጠበቅ እንዲሁም የካርቦን ልቀትን በመቀነስ የልማት ሽግግሩን እውን ለማድረግ ሀገራዊ ራዕይ አለን” ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ በአየር ንበረት ታሳቢ ያደረገ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ መንግስት በአቅም ግንባታና ልምድ ልውውጥ ለማገዝ ያለውን ፍላጎት አንስተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ነመራ ገበየሁ(ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
መንግስት ለስራ ፈጠራ ቅደሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው ማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያበረታታ መዋቅራዊ ሪፎርምን እየተገበረ ይገኛል ብዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ መለከት ሳህሉ በበኩላቸው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የትብብር የኢንቨስትመንት ኢኒሼቲቭ በመንግስት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ትብብር የሚሰሩ ኢንቨስትመንቶችን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።