አየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ የተለያዩ አደጋዎችን ለመቀነስ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ የተለያዩ አደጋዎችን ለመቀነስ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፡- በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ የተለያዩ አደጋዎችን ለመቀነስ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ከ28ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በተዘጋጀው የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የሚኒስትሮች ውይይት ላይ ተሳትፈዋል።
መድረኩ “የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ለሁሉም በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።
ሚኒስትሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ የተለያዩ አደጋዎችን ለመቀነስ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
በተለይ ለሚቲዎሮሎጂ ምልከታ የሚያግዙ ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያ እና መሰረተ ልማት በስፋት በመዘርጋት፤ ወቅቱን የጠበቀ ቦታ ተኮር እና ተደራሽ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የአደጋ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑንም አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የብሄራዊ አደጋ መከላከል ካውንስል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ በመድረኩ የኢትዮጵያን ልምድ ማካፈላቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡