በጥናት ላይ የተመሰረቱ የግጭት መፍቻ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ) ፦በጥናት ላይ የተመሰረቱ የግጭት መፍቻ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የግጭት መንስኤዎችን በመለየት የመፍትሄ አማራጮችን ያመላከተ ጥናት ይፋ አድርጓል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን፤ ጥናቱ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በጥናቱም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የነበሩ የግጭት ክስተቶች ምን እንደነበሩ፣ መንስኤያቸው እና የግጭቱ ተዋንያን እነማን ነበሩ የሚለውን በስፋት የዳሰሰ መሆኑን ተናግረዋል።

የተከሰቱ ግጭቶች መነሻና አባባሽ ምክንያቶችን በዝርዝር የተመለከተ እንዲሁም መፍትሄዎቹን ያመላከተ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በጥናቱ መሰረት የግጭቶች ዋነኛ መነሻ ምክንያት የተለያዩ ቢሆኑም መዋቅራዊ የሆኑና በአግባቡ መፈታት ያለባቸው ችግሮች እንዳሉ ተመላክቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ነጠላ ትርክቶችን በመተው ገዥ የሆኑ የወል ተረክቶችን የማጉላት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።


 

የውይይት ባህል ይበልጥ መዳበር እንዳለበት እና የፖለቲካ ባህሉም ውይይትን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በቀጣይም በጥናቱ ግኝቶች እና ምክረ ሀሳቦች መነሻ እቅድ በማውጣት ተግባራዊ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በጥናት ላይ የተመሰረቱ የግጭት መፍቻ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰላም ግንባታ ዙሪያ መሰል ጥናቶችን በማድረግ የግጭት መንስኤዎችን ቀድሞ መከላከልና አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ያስችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በጥናት ከሚለዩት የግጭት መፍቻ መንገዶች በተጨማሪ ባህላዊ የግጭት መፍቻን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ግጭቶችን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በመንግስት የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው የሰላም ባለቤቱ ህዝቡ በመሆኑ በዚህ ዙሪያም ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ በመድረኩ ተነስቷል።

በመድረኩ በተወካዮች ምክርቤት የሰላምና የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም