የባህርዳር ከተማ የልማት ስራዎች የአመራሩ የትጋት ውጤት ማሳያዎች ናቸው

ባህር ዳር፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፡- የመንግስት አመራሮች በፈተናዎች ሳይረበሹ ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራት እንዳለባቸው በባህርዳር ከተማ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች ማሳያ ናቸው ሲሉ የአራተኛ ዙር ሰልጣኝ የአመራር አባላት ገለጹ።
 
በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ ያለውን ሥልጠና የሚከታተሉ የመንግስት አመራር አባላት በከተማው እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል አቶ ደመላሽ በላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ካለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግርና ማህበራዊ ሚዲያው እያጋነነ ከሚያናፍሰው መረጃ አኳያ ወደ ባህር ዳር መምጣት ጉዳይ አሳስቧቸው ነበር።  

ይሁን እንጂ በከተማዋ ተገኝተው በተግባር የተመለከቱት እንደሚለይ አስታውሰው፤ ሰላማዊ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆናቸውን መታዘብ እንደቻሉ ገልጸዋል።

የከተማዋ አመራር ተቀናጅቶ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች በችግር ውስጥም ሆኖ መስራት እንደሚቻል ያሳዩና በአርአያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን እንደተረዱ ተናግረዋል። 

“በባህር ዳር ከተማ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች ማህበረሰቡ ከመንግስትና ከልማት ስራዎች ያልተነጠለ መሆኑን ማሳያዎች ናቸው“ ያሉት ደግሞ አቶ መሀመድ ካሣ ናቸው።

''በባህር ዳር ከተማ ቆይታችን የመንግስት አመራር አባልና የጸጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆናቸውን እየተገነቡ ያሉት የልማት ስራዎች ምስክሮች ናቸው'' ብለዋል።

ወይዘሮ በየነች ቲንኮ በበኩላቸው፤ የባህር ዳር ከተማ አመራር አካላት ጥረት ወቅታዊ ችግሮችን በመቋቋም በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ እቅዶችን ማሳካት እንደሚቻል የሚያስመሰክር እንደሆነ ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች ስለ ባህር ዳር ከሚናፈሰው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ስራዎች በተግባር በአርዓያነት የሚጠቀሱ የልማት ተግባራትን ማደብዘዝ እንዳልቻሉም ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ወንዳለ ጋሻው እንዳሉት፤ የአመራር አባላት ጉብኝት ከተማዋን የበለጠ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ያግዛል።

የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ማዘውተርያ አገልግሎትን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ የአረንጓዴና ሌሎች በርካታ የልማት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

''ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተሳተፉ የሚገኙት ሰልጣኝ አመራር አባላት በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ  የአረንጓዴና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም