የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት በአነስተኛ መሬት ላይ እያከናወኑ ያለውን የመስኖ ልማት ተሞክሮን ማስፋት ይገባል

ሐረር፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ) ፦የምስራቅ ሐረርጌ ዞን  አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት በአነስተኛ መሬት ላይ እያከናወኑ  የሚገኙትን የመስኖ ልማት ተሞክሮን ለማስፋፋት እንደሚሰሩ  ሰልጣኝ የመንግስት አመራር አባላት ተናገሩ።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የመንግስት  አመራሮች በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳና ግራዋ  ወረዳዎች ላይ የአቮካዶ ችግኝ ማፍያና ማዳቀያ ማእከል፣ በክላስተር እየለማ የሚገኝ የድንች ማሳ፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ የማር ምርትና የከብት ድለባ ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመንግስት አመራር አባላት እንደገለጹት፤ ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት በአነስተኛ መሬት ላይ እየተከናወነ የሚገኘውን የመስኖ ልማት ተሞክሮ ወደ የአካባቢው ለማስፋት እንሰራለን።


 

አስተያየት ከሰጡት አመራሮች መካከል አቶ ቶማሪ ዙካ "ብዙ ከማውራት ይልቅ ብዙ መስራት የተሻለ መሆኑን የዞኑ አርሶ አደሮች መሬት ላይ ባሳዩን የመስኖ ልማት ስራ መገንዘብ ችያለሁ'' ብለዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች መስኖን በመጠቀም በአነስተኛ መሬት ላይ ያከናወኑትን ምርትና ምርታማነትን የማበልጸግ ስራ በአካባቢያቸው ላይም በቁርጠኝነት ለመተግበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

የዞኑ  አርሶ አደር በተበጣጠሰ መሬት ላይ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተገበረው ያለውን አሰራር እንደተመለከቱ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ናስር ሲራጅ ''ይህም መንግስት አርሶ አደሩ ወደ ሃብት እንዲመጣ የያዘውን እቅድ የሚያሳካ ነው'' ብለዋል። 


 

ሌላው አመራር አቶ ተመስገን ታምሬ በበኩላቸው አርሶ አደሩ በአመት ሶስት ጊዜ በመስኖ  ልማት ምርትን በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና  የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በቁርጠኝነት እያከናወኑ ያለው ስራ አበረታች ሆኖ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ፤ የመስክ ምልከታው ዓላማ በዞኑ እየተከናወኑ ያሉትን የግብርናና ሌሎች የልማት ስራዎች በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት ያለመና የስልጠናውም አካል መሆኑን ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም