በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ አፍሪካ 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግዙፉ የንፋስ ሀይል ማመንጫ በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው።
የሚገነባው የንፋስ ሀይል ማመንጫ 600 ሚሊየን ዶላር ወጭ የሚደረግበትና 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ይህንን እውን ለማድረግም የገንዘብ ሚኒስቴር አሜአ ፓወር ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የንፋስ ሀይል ማመንጫው በሶማሌ ክልል አይሻ አካባቢ አሜአ ፓወር በተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያ እንደሚገነባ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የ3 አመታት ጥናት ቀድሞ መደረጉም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
ስምምነቱ በመንግስትና በግል አልሚዎች ማእቀፍ የሚሰራ ትልቁ ኢንቨስትመንት ሲሆን በንፋስ ሀይል ማመንጫ ከምስራቅ አፍሪካ ግዝፉ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ላይ መሰረት ላደረገ የሀይል አቅርቦት ስትራቴጂዋ ተጨማሪ ግብአት ይሆናል፡፡