በሲዳማ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ   የልማት ስራዎች የብልጽግናውን ጉዞ ለማፋጠን የሚያግዙ ናቸው- ሰልጣኝ የመንግስት የአመራር  አባላት 

ሀዋሳ ፤ ህዳር 23 / 2016 (ኢዜአ)፡-  በሲዳማ ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ  የልማት ስራዎች ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠን የሚያግዙ መሆናቸውን በሀዋሳ ማዕከል ስልጠና በመከታተል ላይ የሚገኙ የመንግስት አመራር አባላት ገለጹ። 

ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡት ሰልጣኝ የአመራር አባላቱ በክልሉ የልማት ስራዎችን እንቅስቃሴ ተዘዋውረው  ተመልክተዋል። 

በሸበዲኖ ወረዳ የመስክ ምልከታ ካደረጉ ሰልጣኞች መካከል አቶ ጥላሁን አፈወርቅ በሰጡት አስተያየት ፤ በስልጠናው ያገኙት ልምድና ተሞክሮ  የህብረብሄራዊ አስተሳሰብ እንዲያጎለብቱ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንኑ በአካባቢያቸው በመተግበር ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በሸበዲኖ  የተመለከቱት የጥምር ግብርና ስራ በጠባብ መሬት የተለያዩ ምርቶችን በማምረት የምግብ ዋስትናን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል ልምድ የቀሰምንበት ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

በቡና ልማት ስራም በህብረት ስራ ማህበር የተደራጁ አርሶአደሮች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ አቅም እንዳለ መረዳታቸውና ይህም የሀገር ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ  ገልጸዋል።

ሌላዋ ሰልጣኝ ወጣት ቅድስት ለማ በበኩሏ ፤ከስልጠናው ያገኘችውን እውቀትና ተግባር ተኮር ልምድ ወደ ማህበረሰቡ በማድረስ በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡


 

  በጠባብ  የአርሶ አደር ማሳ ላይ  እየተከናወኑ ያሉት የልማት ስራዎችም በአዲስ አበባ በሌማት ትሩፋት በየግለሰብ ቤት እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ልምድ የሚወሰድባቸው እንደሆኑ ተናግራለች።

ስልጠናው ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ባሉን ጸጋዎች ላይ በጋራ እንድንሰራ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ አቶ ጌታቸው አለህኝ ናቸው። 

በሲዳማ ክልል የተመለከቱት ዝናብ ሳይጠብቁ የሚከናወኑ የግብርና ልማት ስራ ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆኑና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

  አቶ ምትኩ አለማየሁ በበኩላቸው፤  ስልጠናው ከተለያዩ ክልሎች ልምድና ተሞክሮ እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በተለይም በየአካባቢው ያሉ  ጸጋዎችን ለይቶ ለልማት ከማዋል አንጻር የነበሩብንን ክፍተቶች ለይተናል ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በሲዳማ ክልልም በሌማት ትሩፋትና በግብርና ልማት የተከናወኑ ተግባራት በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ ጥምር እርሻን ተጠቅመው በቤተሰብ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ  ስራዎች ያመጡትን  ውጤት በአካባቢያቸው እንዲተገበር ለማድረግ  መነሳሳታቸውን አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ፤ በክልሉ በግብርና፣ በኢንደስትሪና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለተመለከቱት የአመራር አባላት ገለጻ አድርገዋል።

የአመራር አባላቱ ከተመለከቷቸው መካከል፤  በወተት ሀብት ልማትና ዶሮ እርባታ እንደክልል የተገኘው ውጤት፣  የፍራፍሬና የቡና ልማት ስራዎች ፣በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የጨርቃጨርቅ ፣የሳሙናና ሴራሚክ የምርት እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል። 

ከ"ዕዳ ወደምንዳ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን ስልጠና እየተከታተሉ ያሉ የመንግስት አመራር አባላት በሲዳማ ክልል የተለያዩ ወረዳዎችና ሀዋሳ ከተማ የልማት ስራ እንቅስቃሴዎችን ተመልከተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም