በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚካሄደው የወርቅ ማዕድን ልማት ኢትዮጵያ ከዕዳ ወደ ምንዳ እንደምትሸጋገር አመላካች ነው - ሰልጣኝ የመንግስት  አመራሮች 

አሶሳ ህዳር 23 / 2016 (ኢዜአ)፡- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ማዕድን ልማት ኢትዮጵያ ከዕዳ ወደ ምንዳ መሸጋገር እንደምትችል የተግባር  ማሳያ መሆኑን በአሶሳ ማዕከል የአራተኛው ዙር ሰልጣኝ  የመንግስት አመራር አባላት ገለጹ።

የአራተኛ ዙር ሰልጣኝ አመራር አባላት በክልሉ አሶሳ ዞን የሚገኝ የወርቅ አውጪ ኩባንያን እና ባህላዊ አምራቾችን እንቅስቃሴ ዛሬ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ከተሳተፉ አመራር አባል መካከል አቶ መብራቱ ኮሬ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ጥቅም ላይ ሳታውለው ቆይታለች።

በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ጠቁመው፤ ይህንንም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል "በተግባር አሳይቷል" ብለዋል፡፡

በህብረ  ብሄራዊ አንድነት በመነሳት የተፈጥሮ ሀብትን በሚገባ አልምቶ የአገርን እድገት እውን ማድረግ እንደሚቻል አመላካች ማሳያዎች መካከል የወርቅ ማምረቻው ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።  

ሌላዋ የአመራር አባል ወይዘሮ ዝናቧ ርብቃ በበኩላቸው፤ አሁን ማልማት የተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት "አባቶቻችን አገራችንን ጠብቀው ያስታላለፉልን ነው" ብለዋል፡

በክልሉ የሚካሄደው የወርቅ ምርት "ከዕዳ ወደ ምንዳ መሻገር እንደምንችል በተግባር ማሳያ ነው" በማለት ገልጸዋል።

በስልጠናው "ያገኘነውን ልዩ እውቀት እና ጊዜያችንን አሟጠን በመስራት ህዝባችንን ለመደገፍ ከቻልን ከድህነት የማንወጣበት ሁኔታ አይኖርም"  ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኩባንያዎች የተጀመረው ወርቅ የማልማት ጥረት ኢትዮጵያ ወደ መካከለኛ ኢኮኖሚ እንደምትሸጋገር የሚያመላክት መሆኑን የገለጹት አቶ መሃመድ ጣሂር ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ለማልማት "መሰል ልማታዊ ባለሃብቶች በሁሉም ክልሎች ያስፈልጉናል" የሚሉት ደግሞ አቶ ሸረፈዲን ሙሳ ናቸው፡፡

አመራር አባላቱ ዛሬ የጎበኙት የኩርሙክ ወርቅ ማምረቻ ኩባንያ በ500 ሚሊዮን ዶላር ከዓመታት በፊት የተቋቋመ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም