የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር  እንሰራለን - ሰልጣኝ አመራር አባላት

ጅንካ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ) ፦ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ሰልጣኝ የመንግስት አመራር አባላት ገለጹ ።

4ኛው ዙር የመንግስት አመራር አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና በጂንካ ማዕከል እየተሰጠ ሲሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የተወጣጡ ከ700 በላይ አመራሮች ስልጠናውን እየተከታተሉ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አመራር አባላቱ ልዩነቶችን በማጥበብ፣ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የህዝብ ለህዝብ ቅርርቡን ለማጠናከር  የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት አበክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ከቦረና ዞን የተሳተፉት አቶ ዋሪዮ ቦሩ እንደገለፁት፤ የአቅም ግንባታ ስልጠናው አመራሩ በአገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀራራቢ እይታ እንዲኖረው አስችሏል።

አገራችንን ከ"ዕዳ ወደ ምንዳ" ለማሸጋገር የተወጠነውን አገራዊ ራዕይ እድገትና፣ ብልፅግናን ዕውን ለማድረግ የአመራሩ የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በዚህም በአመራሩ ዘንድ የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር ከተቻለ   አገራዊ ሰላም እና አንድነት በጋራ ጥረት ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል ።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጌዴኦ ዞን የመጡት ወይዘሮ አለምፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናው ሁለንተናዊ ዕውቀት ያገኘንበት ነው ብለዋል።

ስልጠናው በአመራሩ ዘንድ ወጥ የሆነ አገራዊ አመለካከት እንዲኖር ከፈጠረው ምቹ አጋጣሚ በተጨማሪ አመራሩ ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ማመንጨት የሚችልበትን አቅም ፈጥሯል። 

ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከስልጤ ዞን የተሳተፉት አቶ ሀያቱ ሙክታር ፥ "የአቅም ግንባታ ስልጠናው ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባትና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል እውቀት እና ክህሎት ያገኘንበት" ነው ብለዋል።

ሀገራችን ብዙ ፀጋዎች አሏት ያሉት አቶ ሀያቱ፤ይህንን ፀጋ በማልማት በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት አመራሩ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን ማስወገድ እና ህዝብ ለህዝብ የሚያቀራርቡ እሴቶችን በማጉላት ህዝቡን ለልማት ማነሳሳት እንዳለበት አንስተዋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከኮንሶ ዞን የመጡት አቶ ታደለ ሮባ፥ ለመፍጠር የታሰበውን  ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ዕውን ለማድረግ የፊት አመራሩ የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

ሀገራዊ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተዛቡ ትርክቶችን ማቃናትና የህዝብ ለህዝብ ቅርርቡን ማጠናከር እንዲሁም  ወንድማማችነትን በማጉላት ረገድ ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አንስተዋል ። 

አመራሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት በሀገሪቱ በሚገኙ ቱባ ባህሎች ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ማጉላት እንዳለበት ያነሱት ደግሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጋሞ ዞን የመጡት የስልጠናው ተሳታፊ አቶ ተስፋዬ አላዛር ናቸው።

በዚህ ረገድ በቱባ ባህሎች ውስጥ ያሉ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነትና ስለ አብሮነት የሚያስተምሩ ባህላዊ እሴቶችን ለትውልዱ በማስተማር ረገድ አመራሩ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ካሉ በኋላ ''እኔምየድርሻዬን ለመወጣት እተጋለሁ'' ብለዋል ።

''አንድነት አቅም ነው፣ አንድነት ልማት ነው ፣ አንድነት አብሮ ማደግ ነው'' ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ለአንድነታችን፣ ለአብሮነታችን እና ለሰላማችን ቅድሚያ በመስጠት እንሰራለን ሲሉም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም