በሲዳማ ክልል ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ሀዋሳ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ) ፦ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር ዋንጫ የአንድ ዓመት ቆይታ ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ።
በሲዳማ ክልል የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በዞኖችና በወረዳዎች ሲዘዋወር የነበረው የህዳሴው ዋንጫ ቆይታ ማጠቃለያ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሀ ግበሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንዳስታወቁት፤ ዋንጫው በክልሉ በነበረው ቆይታ ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ገቢ መደረጉን ጠቅሰዋል።
''ለግድቡ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከተያዘው እቅድ አንጻር ዋንጫው በሲዳማ ቆይታው አላማውን ሙሉ ለሙሉ አሳክቷል'' ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ትውልድን በአንድነት ያስተሳሰረ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በተለይ ከለውጡ ወዲህ መንግሥት ከግድቡ ጋር የነበሩ ችግሮች እንዲወገዱ በማድረጉ አሁን ላይ ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ሁሉንም አነቃቅቷል ብለዋል።
የዋንጫው መዘዋወር በግድቡ ዙሪያ ህብረተሰቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።
በዚህ ረገድ የክልሉ ህዝብም በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና ቦንድ በመግዛት ላሳየው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ርእሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ ዋንጫው በክልሉ በነበረው የአንድ ዓመት ቆይታ በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች መዘዋወር መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ በነበረው ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ እስካሁን በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ የተበረከተ ሲሆን በቀጣይም የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር እስከ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግበሩ ላይ የተሳተፉ የንግዱ ማህበረሰብና ባለሀብቶች ከ100 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ለግድቡ ግንባታ ቦንድ ለመግዛት ቃል ገብተዋል።
ቃል ከገቡት መካከል የሀዋሳ ነዋሪ አቶ አለቃ ከበደ ከዚህ በፊትም ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው አሁንም በራሳቸውና በባለቤታቸው ስም የ500 ሺህ ብር ቦንድ እንደሚገዙ አስታውቀዋል።
ከክልሉ የመንግስት ሰራተኞች መካከል አቶ ሽታዩ ዩመራ በሰጡት አስተያየት ለግደቡ ግንባታ መሳካት ሶስት ጊዜ በወር ደሞዛቸውን ቦንድ በመግዛት መሳተፋቸውን ጠቅሰው ዛሬም በማጠቃለያ መርሃ ግበሩ ላይ በመገኘት የ3 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን ዳግም ማሳረፋቸውን አስታውቀዋል።
ግድቡን ከዳር ለማድረስ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ገልጸው እሳቸውም በሚችሉት ሁሉ ተሳትፎአቸውን ለማስቀጠል እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል።
የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መድሀኒት ከበደ በበኩላቸው ለግድቡ ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ ባሻገር ስለግድቡ የሚነሱ አሉታዊ አስተሳሳቦችን በሀሳብ በመሞገት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ይናገራሉ።
በብዙ ውጣ ውረድ፣ ከውስጥም ከውጭም ጫና እየበዛብን የህዳሴውን ግድብ ውሃ ሞልተን ኃይል እንዲያመነጭ አድርገናል ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በቀጣይም አንድነታችንን በማጠናከር ግድቡን ከፍጻሜ እናደርሰዋለን ብለዋል።
በመርሃ ግበሩ ላይ የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በቆይታው የተሳካ ውጤት እንዲመዘገብ የበኩላቸውን ለተወጡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ለባለሀብቶችና ለግለሰቦች የክልሉ መንግሥት የእውቅና ሠርተፊኬት አበርክቷል።
ዋንጫው በዘንድሮው 18ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክብረ-በዓል ላይ በይፋዊ ፕሮግራም ተረኛ ለሆነችው ለጅግጅጋ ከተማ ተላልፎ እንደሚሰጥም ተገልጿል።