ለሀገራዊ አንድነት ብዝሃነትን ጠንካራ መሰረት በማድረግ የበለጸገችና ለሁላችንም የምትመች ሀገር መገንባት አለብን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ አንድነት ብዝሃነትን ጠንካራ መሰረት በማድረግ የበለጸገችና ለሁላችንም የምትመች ሀገር በጋራ መገንባት አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

18ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን  "ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ   በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።


 

እለቱን በማስመልከትም በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ የባህል ፌስቲቫል ተካሒዷል፡፡

በመድረኩ ላይ  መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚከበረው በብዝሃነት አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለሀገራዊ አንድነት ብዝሃነትን ጠንካራ መሰረት በማድረግ የበለጸገችና ለሁላችንም የምትመች ሀገር በጋራ መገንባት አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለልዩነት ምክንያት የሆኑ ነጠላ ትርክቶችን በመተው አንድነትን የሚያጠናክሩት  ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፤ የዕለቱ መከበር ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የባህል ትስስር በመፍጠር ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።



የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በዚህ መልኩ መከበሩ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ለባህል ትስስርና ለጋራ የሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

18ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚከበር ይሆናል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም