የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም የመገንባት ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ

153

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፡- የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም የመገንባትና የሰው ሃይል የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገለጹ።

ለአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ከህዳር 17 ቀን  2016 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።


 

የስልጠናው ትኩረትም ተቋማዊ ሪፎርም፣ የፖሊስ ስነ-ምግባርና የለውጥ አመራር፣የተቋም ግንባታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ ነው።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፤ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚቻለው ጠንካራ የፖሊስ ተቋምና አመራር መፍጠር ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራርና አባላት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እያደረጉት ላለው የላቀ ሚና አመስግነው በቀጣይም ለተሻለ አፈፃፀም እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

ለዚህም የፖሊስን አቅም በሁሉም መልኩ ማጎልበትና ለወንጀል መከላከል እና የምርመራ ስራ የሚያግዙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጠንካራ የፖሊስ ተቋም የመገንባትና የሰው ሃይል የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ስልጠናው የተቋሙን ተልዕኮ መነሻ በማድረግ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይነት እስከ አባሉ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮችም በቀጣይ ለተሻለ ስራ የሚያዘጋጅ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸው ለተሻለ ስራ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም