ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በቂ ትምህርት ወስዳለች - መሀመድ አብዱላኢ ሙሳ

139

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ ከተከናወነው ተግባር ጅቡቲ በቂ ትምህርት ወስዳበታለች ሲሉ የሃገሪቱ የአካባቢ ጥበቃና የዘላቂ ልማት ሚኒስትር መሀመድ አብዱላኢ ሙሳ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው ኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ያዘጋጀችውን አረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ/ፓቪሊዮን የሃገራት መሪዎች፣የጉባኤው ተሳታፊዎች እየጎበኙት ነው።

ፓቪሊዮኑን የጎበኙት ሚኒስትር መሀመድ አብዱላኢ ሙሳ እንደተናገሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ኢትየጵያ ባለፉት አምስት አመታት በአረንጎዴ ልማት ያከናወነቻቸው ተግባራት ትልቅና የሚያስደንቁ ናቸው።

በቀጣይም ጅቡቲ በኢትዮጵያ የተከናወነውን የአረንጎዴ ልማት ተግባራዊ ለማድረግ በአገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር በኩል የተጠናከሩ ስራዎችን በትኩረት እንደምትሰራ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገሮች መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ በትራንስፖርትና በኤሌክትሪክ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ጥበቃ ላይም በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጎዴ ልማት ስራ ለጅቡቲ በርካታ ችግኞችን በመለገስ የአረንጎዴ አሻራ እንዲስፋፋ ያደረገችው አሰተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም