የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መፃህፍትን እያሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መፃህፍትን እያሰራጨ ነው

ሶዶ፣ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መፃህፍት ስርጭት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሐብታሙ ታደሰ እንዳሉት ቢሮው ከጥቅምት 28 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ የ2ኛ ደረጃ የመማሪያ መፃህፍት ስርጭት እያካሄደ ነው።
ከዚሁ የመማሪያ መጻህፍት ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት ቢሮው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።
በክልሉ ከ400 ሺህ በላይ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች መኖራቸውን የገለፁት አቶ ሐብታሙ፤ ከዚህ ቀደም የተሰራጨውን ጨምሮ አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ስርጭት ተማሪዎቹን በተገቢው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በቀጣይም አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ እስኪዳረስ ድረስ ስርጭቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ይህም በሚቀጥሉት 30 ቀናት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የሚዳረስ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አሁን ላይ ታትሞ የመጡ የትምህርት ዓይነቶች ከወላይታ ሶዶ ማዕከል በክልሉ ለሚገኙ የዞን መዋቅሮች የማሰራጨት ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ በመገኘት መጻህፍቱን ሲረከቡ ካገኘናቸው መካከል የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ካሳሁን ደባሶ በበኩላቸው የተመደበላቸውን 113 ሺህ መፃህፍትን ተረክበዋል።
ሚኒስቴሩና ቢሮው በመቀናጀት የመፃህፍት እጥረት በመፍታት የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ እያደረጉ ያለው ጥረት መልካም ጅማሮ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ አቶ ተመስገን ሌንጫ በሰጡት አስተያየት የመጣውን መጻህፍት በዞኑ ላሉ ትምህርት ቤቶች በፍጥነት ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከመማሪያ መጻህፍት እጥረት የተነሳ የነበረውን ጥያቄ ለመፍታት አሁን ላይ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተማሪዎችና መምህራን ይህን ታግዘው ዓላማቸውን ከግብ እንዲያደርሱ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።
በሶዶ መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ፅናት ምትኩ ከመማሪያ መጽህፍት እጥረት የተነሳ ጥያቄ ላይ እንደነበሩ ጠቅሳ፤ አሁን ላይ ይህን ለማስተካከል እየተደረገ ያለው ጥረት የመማር ሞራላቸውንም የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግራለች።
ተማሪ ጽናት አክላም "የተሰራጨው በቂ ባይሆንም የጊዜ አጠቃቀማችንን አስተካክለን ጥሩ ነጥብ ለማምጣት እንጥራለን" ብላለች።