ኢትዮጵያ በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚታይና የሚቆጠር ውጤት ይዛ ቀርባለች - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ አውደ ርዕይ ላይ የሚታይና የሚቆጠር ውጤት ይዛ መቅረቧን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የግብርና ዘርፎች ላይ ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶችና ተሞክሮ የሚያሳይ አውደ ርዕይ ይዛ ቀርባለች።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ኢትዮጵያ በጉባኤው ይዛ የቀረበችውን አውደ ርዕይ በተመለከተ የሀገራት መሪዎች መጎብኘታቸውንና ያሳደረባቸውን ተነሳሽነት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
  
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ለዕይታ ይዛ የቀረበቻቸውን የአረንጓዴ አሻራ ውጤቶች በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙ የሀገራት መሪዎች መጎብኘታቸውንና በተመለከቱትም ነገር መደነቃቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ በአውደ ርዕዩ ይዛ የቀረበችው የአካባቢ ጥበቃ ውጤት የአመራር ቁርጠኝነት የሚታይበት መድረክ ስለሆነ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት መሪዎች ጭምር ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያከናወነች ባለው ተግባርና ባስገኘችው ውጤት መደነቃቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም መሪዎቹ በጉባኤው ላይ ባደረጓቸው ንግግሮች ሁሉ በዘርፉ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማሳያነት ሲጠቀሙበት ተስተውሏልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አክለውም በቀጣይ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በልዩነት ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው አረንጓዴ አሻራ ይሆናል ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሳየችው ተነሳሽነትና ያገኘችው ውጤት ለዓለም ከፍተኛ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ያሳያል ሲሉም አክለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ እና የስራ ዕድል የሚፈጠርበት ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ውጤት ተጨባጭ መሆኑን በቡና፣ በስንዴ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ የተገኘው ውጤት ጥሩ ማሳያዎች ናቸውም ብለዋል ወይዘሮ ጫለቱ።

የአካባቢ ጥበቃ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ድሮም የኢትዮጵያ ባህል የነበረ ነገር ግን በአመለካከት ላይ በነበረ ችግር ምክንያት አረንጓዴ ነገርን ማጥፋት ላይ ዝንባሌዎች ይታዩ ነበር ብለዋል።
  
በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የህብረተሰቡን አመለካከት ከመንቀል ወደ መትከል ያሸጋገረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም አሁን ላይ ባህል ሆኖ በየዓመቱ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት እያደረገች ያለችው ድጋፍ እንደ አንድ ተሞክሮ የሚጠቀስ ነውም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግበር የተለያዩ ፍራፍሬዎች በሀገር ውስጥ ገበያ እንደልብ እዲገኙ ከማስቻሉም በላይ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ግብርናን ትራንስፎርም ማድረግና በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ መሳካት የሚችለው በአረንጓዴ አሻራ ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባልም ነው ያሉት ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው። 

አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የትውልዶች ውጤታማነትን በግልጽ ማሳየት የሚችል መሆኑን ገልጸው ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተስማማ ከተማ መፍጠር እንዲቻልም መርሃ-ግብሩ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት። 

የአፈር ጥበቃ ስራዎች የህይወታችን መሰረቶች በመሆናቸው የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማትና ዝናብን ከመሳብ አኳያ በአጠቃላይ በአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴዎች ላይ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም