ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሳየችው ለውጥ ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሳየችው ለውጥ ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሳየችው ለውጥ ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ በዚህ መርሃ ግብር ከ30 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከሏንም ጠቅሰዋል።
በዱባይ እየተካሔደ በሚገኘው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ተሞክሮዎቿን የምታካፍልበት አውደ ርእይ/ፓቪሊዮን/ በሃገራት መሪዎች፣ በጉባኤው ተሳታፊዎች በመጎብኘት ላይ ነው።
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ አውደ ርእይ/ፓቪሊዮን/ የጎበኙት ዋና ጸሀፊው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ከአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንሶች እና መገናኛ ብዙሃን ገለጻ በላይ ችግሩን በተግባር ተከስቶ ማየታቸውን አስታውሰዋል።
ቀጣናው በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት የጎርፍ እና የድርቅ አደጋዎች ከማስተናገዱ ጋር በተያያዘ ሀገራቱ ችግሩን ለመፍታት የራሳቸውን መፍትሄ መውሰዳቸውን ሲገልጹ ለዚህም የኢትዮጵያ ተሞክሮ በአረአያነት መጠቀሱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
የዱባዩ ጉባኤ ችግሩን ለመቋቋም የተደረጉ ተሞክሮዎች የሚቀርቡበትና ግብዓት የሚወሰድበት ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችው መካነ ርዕይ ችግሩን ለመፍታት የፈጠረችው የህዝብ ንቅናቄው ወደ ውጤት መቀየሩን ያረጋገጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተትን ለመቅረፍም ከ30 ቢሊየን በላይ ዛፎችን መትከሏን ተናግረዋል።
ይህም ከዓለም የገንዘብ ተቋማት ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ ሳትሻ መሪዎቿ ህዝብን በማነቃነቅ ለአካባቢ ጥበቃ በማዋል ለቀጣናው ሀገራት ጭምር ዛፎችን መስጠታቸውን ተናግረዋል።
አፍሪካ ባልፈጠረችው የተዛባ ተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር መዳረጓን ከማስረዳቷም ባለፈ ኢትዮጵያ ከኢጋድ ጋር በመሆን አፍሪካን ወክላ ለጉዳቱ ማካካሻ ፈንድ በማምጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጓን ጠቅሰዋል።