በባህር ዳር ከተማ 392 ሚሊዮን ብር በሆነ በጀት የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

ባህር ዳር ፤ ህዳር 23 / 2016 (ኢዜአ)፡- ባህር ዳር ከተማን ውበና  ጽዱ ለማድረግ በ392 ሚሊዮን  ብር  የተጀመሩት  የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ   በመጪው  ጥር ወር ተጠናቀው  ለአገልግሎት እንደሚበቁ  ተገለጸ። 

የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ አለሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  በግንባታ ላይ የሚገኙት የሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች  83 ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ የባህር ዳር ከተማን ጽዱ፣ ውብና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአለም ባንክ የከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳንቴሽን ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ እየተሰሩ እንደሚገኙ   ገልጸዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል የጋራ መኖሪያ ቤቶች  “ሲፍቲ ታንኮሮች” እና የከተማዋን የፍሳሽ አወጋገድ ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዙ  ግንባታዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከተማዋ አሁን ላይ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ተመራጭ እየሆነች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎቿ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ የነዋሪዎችን ጥያቄ ለሚመልሱ ፕሮጀክቶቹ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል። 

የሳንቴሽን ፕሮጀክቶቹ ግንባታ እየተካሄዱ ያሉት በገበያ አካባቢዎች፣ በተሽከርካሪ መናኸሪዎችና ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው ስፍራዎች  መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ይህም በተለይ የከተማዋን ጽዳት ለማስጠበቅ ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።

በአገልግሎቱ የሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋው አካልነው በበኩላቸው፤ የባህር ዳር ከተማን የሳንቴሽን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት  በውጭ ኩባንያ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።


 

በጥናቱ ግኝት መሰረትም  የ83 የሳንቴሽን ፕሮጀክቶች ግንባታን በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ እንደተጀመሩ ጠቅሰው፤  አሁን ላይ ግንባታቸው ከ75 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ እስከ ጥር ወር 2016 ዓ.ም መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ አመልክተው፤ ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡም ለተደራጁ ወጣቶች በማስረከብ በአነስተኛ ክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣይም የከተማዋን የሳንቴሽን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት  ጥናቱን መሰረት በማድረግ እንደሚሰራም አቶ ተስፋው አመልክተዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም