በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጸረ ሙስና ትግልን ስኬታማ ለማድረግ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል 

ሆሳዕና፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦የጸረ ሙስና ትግሉ ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ማህበረሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው አሳሰቡ ።

"ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው! በጋራ እንታገለው!! " በሚል መሪ ሃሳብ  የጸረ ሙስና ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ  በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በመድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በክልሉ ብልሹ አሰራርና የሙስና ድርጊቶችን ለመቀነስ ብርቱ ትግል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የመንግስት አገልግሎትን በዝምድና፣ በሙስናና በመሰል ተደግፎ የሚሰጥ ከሆነ ብልሹ አሰራርን እያስፋፋ መንግስትንም ሆነ ህዝብን ለከፋ አደጋ ይዳርጋል ብለዋል ።

ሙስናና ብልሹ አሰራር ዕድገትን እያቀጨጨ ለልዩነቶች ምንጭ በመሆኑ  ችግሩን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት  በየደረጃው ያለው የመንግስት አመራርና ማህበረሰቡ  ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የሀይማኖትና የትምህርት ተቋማት በስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት በማሳካት ረገድም የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል ።


 

የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ማሞ ቴጌ በበኩላቸው ሙስናና ብልሹ አሰራር በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ግንዛቤን የማሳደግ ስራ የኮሚሽኑ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ማህበረሰቡ ጥረቶችን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ጠይቀው በተለይም አገልግሎቶችን በእጅ መንሻ ለመፈጸምም ሆነ ለማስፈጸም ከሚደረግ ጥረት በመቆጠብ የትግሉ አካል ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት 100 ቀናት ውስጥ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኮሚሽኑ ጥናትና ክትትል በማድረግ ተጋላጭ መስሪያ ቤቶች መለየቱን ጠቁመው በቀጣይም በህግ የሚጠየቁበት ስርዓት ለማበጀት ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።


 

ከተሳታፊዎች መካከል በክልሉ ጤና ቢሮ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤልሳቤጥ በጋሻው ሙስናና ብልሹ አሰራር ለዕድገት ጸር የሆነ አለፍ ሲልም ለሰላም እጦት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል ።

ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውሮችና ሌሎች ጎጂ ተግባራት በቢሮ ደረጃ መኖራቸውን አንስተው በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነም አንስተዋል።

በዞኑ የሚስተዋሉ የሙስናና የብልሹ አሰራሮችን ከጅምሩ ለመግታት ጥረቶች መኖራቸውን  የተናገሩት በጉራጌ ዞን አስተዳደር የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና የስራ  ሂደት አስተባባሪ  አቶ ጀማል አህመድ ናቸው።

በባለፉት ሶስት ወራት በተሰራ ስራ ከ340 ሄክታር በላይ በከተማና በገጠር በህገ ወጥ መንገድ የተወረሩ የመሬት ይዞታዎችን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የተመዘበረ የህዝብና የመንግስት ሀብት ማስመለስ መቻሉን አብራርተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሱርሞሎ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም