“ኑ ባሌን ጎብኙ” የ6 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

ሮቤ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ) ፦ “ኑ ባሌን ጎብኙ” በሚል መሪ ሐሳብ የባሌን የቱሪዝም መስህቦች ማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የ6 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዛሬ በሮቤ ከተማ ተካሄደ፡፡

ውድድሩን ያዘጋጁት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽንና ሳዲያ መልቲ ሚዲያ በመተባበር ነው። 

ሩጫው በተለይ በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት የትምህርትና የባህል ተቋም/ዩኔስኮ/ የተመዘገበውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል። 

እንዲሁም ሌሎች በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችን ለማስተዋወቅና ለማልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም እንዲሁ፡፡

ሩጫውን ያስጀመሩት የባሌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የባሌ ዞን የብዙ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ ባለቤት በመሆኑ ዘርፉ የዞኑንም ሆነ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲደግፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል። 

በተለይም የአያሌ አዕዋፋት፣ አራዊትና የተለያዩ መልክዓ ምድርን ያቀፋው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መደረጉ የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል። 

አስተዳዳሪው እንዳሉት ዞኑ የአያሌ የመስህብ ስፍራዎች መገኛ ቢሆንም በሚገባ ለምቶ ለአገር መስጠት የሚገባውን አበርክቶ በመስጠት ረገድ ውስንነቶች አሉት። 

ዛሬ የተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫም በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅና ለማልማት ማነቃቂያ እንዲሆን ታስቦ ነው።

የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው አስተዳደሩ ሮቤን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ በተጓዳኝ የቱሪዝምና የንግድ ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል። 

ባለኃብቶች ከተማዋ ያላትን ምቹ እድሎች በመጠቀም በሆቴሎችና ሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። 

"ክልሉ የብዙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህብ ባለቤት ቢሆንም ዘርፉ የክልሉን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲደግፍ ለማድረግ ብዙ ስራዎች ይቀራሉ ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር  ወይዘሮ ለሊሴ ዱጋ ናቸው"

ኮሚሽኑ በክልሉ የሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችን በማልማትና እንዲተዋወቁ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መሪ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን በማከል። 

በባሌ ሮቤ የተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫም የቱሪዝም መስህቦችን የማስተዋወቅና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማነቃቃት ዓላማ ያለው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

ውድድሩን በወንዶች  ብርሃኑ ጌታሁን  በሴቶች ደግሞ አበራሽ ከበደ ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቀዋል ። 

ለሩጫው አሸናፊዎች የገንዘብ  ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። 

 ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ በቋሚነት መመዝገቡን በማስመልከት ህዳር 25 ቀን 2016ዓ.ም የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በባሌ ሮቤ የሚካሄድ የእውቅና መርሃ ግብር እንደሚዘጋጅ ታውቋል።

የዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫው የዚሁ መርሃ ግብር አካል መሆኑንም ከዞኑ አስተዳደር መረጃው  ያመለክታል።

የባሌና ምስራቅ ባሌ ዞኖች የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻ፣ የድሬ ሼህ ሁሴን እንዲሁም ጥቅጥቅ የሀረና ጥብቅ ደንና ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም