በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው- ዶክተር አህመዲን ሙሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው- ዶክተር አህመዲን ሙሀመድ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን ሙሀመድ፤ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ የውይይት መድረኮች የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የሰላም ጉዳይ፣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት በህዝቡ በተደጋጋሚ የተነሱ ጥያቄዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ስር የሚመራው ኮማንድ ፖስትም በክልሉ አዲስ የተደራጀውን አመራር በማገዝ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በክልሉ ከላይ ጀምሮ እስከ ቀበሌ የተዋቀረው አመራር በተቀናጀ መልኩ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ሌት ከቀን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ዘላቂ ሰላም የመፍጠርና ልማትን የማስቀጠል እንዲሁም በየሴክተሩ የህዝብን ጥያቄዎች በሂደት የመመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ የተደራጀው የክልሉ የፖለቲካና የጸጥታ አመራር በአገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ ሥልጠናዎች ላይ በመሳተፍ ህዝብን ለማገልገል የሚያስችል ተነሳሽነትን ልምድ ማግኘቱንም አንስተዋል።
በመድረኮቹ በመልካም አስተዳደር፣ በልማት፣ በኑሮ ውድነት፣ በሰላምና ደህንነትና ሌሎችም ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን በቅጡ በመረዳት ወደ ተግባራዊ ምላሽ መገባቱንም ተናግረዋል።
በመሆኑም በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በየደረጃው የተመደቡ የስራ ኃላፊዎች የተጀመሩ በጎ ስራዎችን በማስቀጠል ህዝብ በጉድለት የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑንም ዶክተር አህመዲን አረጋግጠዋል።
የክልሉን ዘላቂ ሰላም በማጽናት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ህዝቡ እገዛና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።