በዳሰነች ወረዳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ እገዛ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በዳሰነች ወረዳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ እገዛ ተደረገ

ጂንካ፤ ህዳር 23 /2016 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደና ሌሎች ከፍተኛ አመራር አባላት በወረዳው በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን የተመለከቱ ሲሆን፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚቻልበት ዙሪያ ከተጎጂዎች ጋር ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ፤ የኦሞ ወንዝ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ በአርብቶ አደሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በክልሉ የተቋቋመው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚቴ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ የሰብአዊ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የምግብ ዱቄት፣ አልባሳትና ምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደርገዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የከለዋ መንደር ነዋሪ አቶ ሎረኝ ሰረት በሰጡት አስተያየት፤ የኦሞ ወንዝ መደበኛ የመፋሰሻ አቅጣጫውን ስቶ ባልተጠበቀ ሁኔታ አካባቢያቸውን በጎርፍ ማጥለቅለቁን አውስተዋል።
በዚህም ምክንያት የመኖሪያ አካባቢቸውን ለቀው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተው፤ መንግስት የሰብአዊ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት አመራር አባላት የገጠማቸውን ችግር ለመመልከት በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የመርመርቴ መንደር አርብቶ አደር ሊዮን ጳዮ በበኩላቸው፤ በአካባቢው የተከሰተው ጎርፍ ለችግር አጋልጦናል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የዕለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው፤መንግስት በዘላቂነት እንዲያቋቁማቸው ጠይቀዋል።