የታዳሽ ሃይል አቅርቦትን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ለቀረበው ጥሪ የበርካታ አገራት ድጋፍ አገኘ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 23/2016 (ኢዜአ)፦ የታዳሽ ሃይል አቅርቦትን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ለቀረበው ጥሪ የበርካታ አገራት ድጋፍ ማግኘቱ ተገለጸ።

በዱባይ እየተካሄደ ባለው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የአገራት መሪዎች የታዳሽ ሃይል አቅርቦትን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሶስት እጥፍ ለማሳደግ መስማማታቸውን ተዘግቧል። 

ከአንድ መቶ አስር በላይ የሚሆኑ የአገራት መሪዎች እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 የታዳሽ ሃይል አቅርቦትን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ለቀረበው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ቮንደር ሊይን ገልጸዋል።

መንግስታትም ሆኑ ግዙፍ ኩባንያዎች ከፍ ያለ መዋእለ ንዋያቸውን ለዚሁ አላማ መሳካት ያውላሉ ወይ  የሚለው ጥያቄ መመለስ እንደሚኖርበት አጽንኦት የሰጡት ፕሬዝደንቷ የግብአት አቅርቦት፣ የዋጋ ጭማሪ፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም የፕሮጀክቶች አፈጻጸምን የተመለከቱ ጉዳዮች ከውሳኔው በኋላ መፍትሄ የሚፈለግላቸው ይሆናል ብለዋል።


በጉባኤው የሚነሳው ሃሳብ የሁለት መቶ አገራት ይሁንታ የሚፈልግ መሆኑን የተነገረ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ጥሪውን በግንባር ቀደምነት የተቀበሉ ናቸው።

ቻይናና ህንድ በይፋ ሃሳባቸውን ባይገልጹም በካይ የሚባሉትን የድንጋይ ከሰልና የነዳጅ ዘይት የሃይል ምንጮችን በመቀነስ  የታዳሽ የኃይል አማራጮችን በ2030 በሶስት እጥፍ ማሳደግ በሚለው ሃሳብ ዙሪያ የመስማማት አዝማሚያ ማሳየታቸውን ተገልጿል።

ደቡብ አፍሪካ፣ ቪየትናም፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ካናዳ፣ ቺሊና ባርባዶስ ሃሳቡን በይፋ መቀበላቸውን ከገለጹ አገራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን የኢነርጂ ዎርልድ ዘገባ ያመለክታል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም