ኢትዮጵያ በትብብር ከቀጣናው አገራት ጋር የመልማት ጽኑ ፍላጎቷን ማስገንዘብ ተችሏል - አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በትብብር ከቀጣናው አገራት ጋር የመልማት ጽኑ ፍላጎቷን ማስገንዘብ ተችሏል - አቶ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት የመሪዎች ጉባኤ በትብብር ከቀጣናው አገራት ጋር የመልማት ጽኑ ፍላጎቷን ማስገንዘብ ችላለች ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 28) ጎን ለጎን የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት የመሪዎች ጉባኤ መካሄዱን ገልጸዋል።
በጉባኤው በኢትዮጵያ በኩልም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በመወከል መሳተፋቸውን አብራርተዋል።
በመድረኩም የራሳቸው የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት በልማት ሥራና በአካባቢ የአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ተጨማሪ ጫና ያላባቸው መሆኑን ኢትዮጵያ አቋሟን እንዳሳወቀች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከምታንቀሳቅሰው ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም አኳያ የራሷ የባህር በር አለመኖሩ የሚያመጣባትን ጫና ለመቋቋም የበለጠ ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን ማስረዳት ተችሏል ብለዋል።
በመሆኑም የባህር በር የሌላቸው አገራትም ትብብር በማጠናከር ዓለም አቀፍ የልማት አጋርና መንግሥታት ተጨማሪ ትኩረት እንዲሰጣቸው ማስገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም፤ ከቀጣናው አገራትና ከዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በባህር በር ላይ በትብብር የመሥራት ፍላጎት ያላት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የምትጠቀመውን የጅቡቲ የባህር በር አገልግሎትም በምሳሌነት የሚጠቀስ የትብብር ማሳያ መሆኑን መግለጽ እንደተቻለም ገልጸዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ በመልካም ጉርብትናና ትብብር መንፈስ ከቀጣናው አገራት ጋር ለመልማት ፍላጎት እንዳላት ማስረዳት መቻሉን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የቀጣናው ጎረቤት አገራትም የኢትዮጵያን የትብብር ተነሳሽነት የመቀበል ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ማስገንዘብ ተችሏል ብለዋል።
በርካታ አገራትን እያስጨነቀ የሚገኘው እዳም የራሳቸው የባህር በር በሌላቸው ላይ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን አብራርተዋል።
በታዳሽ ኃይልና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ ከእራሷ አልፋ የጎረቤት አገራት ለማስተሳሰር ያደረገችውን ጥረትም ማስረዳት እንደተቻለ ጠቁመው፤ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወደ ሥራ ሲገባም ለቀጣናው አገራት መተሳሰር ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጠር መግለፃቸውን አንስተዋል።
በመድረክም የራሳቸው የባህር በር የሌላቸው አገራት ዓለም አቀፍ ቲንክ ታንክ ግሩፕ እንዲቋቋም የጋራ አቋም ተይዟል ብለዋል።