ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተመድን የአየር ንብረት ለውጥና የምግብ ዋስትና አጀንዳዎች የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና አጀንዳዎችን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን በኮፕ 28 ጉባኤ አሳይታለች ሲሉ የኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ተወካይ ናሙኮ ኮቪች ገለጹ።

የኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ተወካይ ናሙኮ ኮቪች ኢትዮጵያ በኮፕ28 ጉባኤ በራስ አቅም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያከናወነችውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አካፍላለች ብለዋል።

በዚህ ተሞክሮ ሀገሪቷ ችግሮችን የሚቋቋም ጠንካራ የተግባር ስራዎች በማከናወን ላይ እንደምትገኝ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እንዲሁም አለም አቀፍ የዘርፉን አጀንዳዎች በሙሉ አቅም ለመተግበር ተጨባጭ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኗንም እንደተረዱ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ በአረንጓዴ ልማት ማዕቀፍ 50 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እያከናወነች ያለችው ተግባር በተሞክሮነት እንደሚወሰድ አውስተው ይህም ሁለትዮሽ ጥቅም ያለው መሆኑን ነው ያብራሩት።

ከሚተከሉት ችግኞች ገሚሱ ለምግብነት የሚውል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ጎን ለጎን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተግባራዊ እርምጃ መሆኑንም አብራርተዋል።

እንደ ሌማት ትሩፋት ያሉ መርሐግብሮችም በዚህ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸውና ቀጣይነት ያለው የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለመከወን የተያዘውን ሀገር አቀፍ ውጥን ኢትዮጵያ በኮፕ 28 ጉባኤ ማሳየቷን አስገንዝበዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም