የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ እያስቻለ ነው

ሮቤ ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፡-  የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑን የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ገለጸ። 

ማዕከሉ በተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማት እንክብካቤ ላይ በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ እያካሄደ የሚገኘው ሥራ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል። 

በምርምር ማዕከሉ እየተከናወኑ ከሚገኙ ምርምሮች መካከል የአፈር ለምነት ማሻሻል፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ የንብ ማነብና የአፈር መሸርሸር መቀነስ ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆኑም ተመልክቷል። 

በሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈር ለምነት ተመራማሪ አቶ ሙሉጌታ እሸቱ እንዳሉት፣ የማዕከሉ የምርምር ስራዎች አርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡና ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። 

በተለይ በአፈር መሸርሸርና ጎርፍ ሳቢያ ስጋት ሆነው የቆዩ የተፋሰስ ልማቶች ላይ በተሰሩ ሥራዎች መሬቱ ዳግም ለልማት እንዲውል እየተደረገ ነው ብለዋል። 


 

በተለይ የምርምር ማዕከሉ ከ500 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በአጋርፋ ወረዳ እያከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን በማሳያነት አንስተዋል። 

አቶ ሙሉጌታ እንዳሉት፣ በማዕከሉ እየተከናወኑ ከሚገኙ ምርምሮች መካከል የአፈር ለምነት ማሻሻል፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ የንብ ማነብና የአፈር መሸርሸር መቀነስ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። 

አርሶ አደሩ በተለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ ያገኘው የቁሳቁስ ድጋፍና የዕውቀት ሽግግር ለፋብሪካ ማዳበሪያ ያወጣ የነበረውን ወጪ እንደሚቀንስ ተናግረዋል። 

በዘመናዊ የቀፎ ዝግጅትና የጓሮ አትክልት ልማት ላይ ግንዛቤ በማግኘት ከሚያደርገው መደበኛ ልማት በተጓዳኝ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል። 

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተማሮ ገልገሎ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ በ8 የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን እያካሄደ ነው። 

ማዕከሉ በተለይ ከዚህ ቀደም በሰብል ልማት፣ የጥራጥሬና የእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት በማድረግ የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት በተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

አቶ ተማሮ እንዳሉት፣ የምርምር ማዕከሉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችም አርሶና አርብቶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱ በራሱ ማሳ ላይ በማዕከሉ ተመራማሪዎች ከሚደረገው ሙያዊ ምክር በተጓዳኝ የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን በማዘጋጀት እርስ በርስ እንዲማማሩ እየተደረገ ነው። 

አስተያየታቸውን ከሰጡ የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አበበ ከበዳ፤ ከማዕከሉ የሚለቀቁ ምርጥ ዘርና የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተከታትለው እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ከማዕከሉ በድጋፍ ያገኙትን ዘመናዊ የንብ ቀፎ በግቢያቸው ውስጥ በማዘጋጀት ከመደበኛ የሰብል ልማት በተጓዳኝ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል። 

በተለምዶ ሲያካሄዱ በነበረው የተፋሰስ ልማት ሥራ የማዕከሉ ተመራማሪዎች ያገኙትን ሙያዊ ድጋፍ ተጠቅመው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለልማት እያዋሉ መሆኑን አክለዋል። 

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከ97 የሚበልጡ የሰብል ዝሪያዎችና የእንስሳት መኖ ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ውጤቶችን ለአርሶ አደሮች ማድረሱን ከምርምር ማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም