በአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣ መጀመሩን ኮሚሽኑ አስታወቀ

ሰመራ፤ ህዳር 22/2016 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣ ዛሬ በሰመራ ሎጊያ ከተማ መጀመሩን የኢትየጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ዛሬ በሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር በተካሄደ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣም 36 ተወካዮች መለየታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በመረጣው ሂደት ከዘጠኝ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 180 ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን 36 የህብረተሰብ ተወካዮችም ተመርጠዋል።


 

የተመረጡት የህብረተሰብ ተወካዮች የጎሳ መሪዎች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የንግድ ማህበረሰቡና ተፈናቃዮች ማካተታቸው ተገልጿል።

በሰመራ ሎጊያ ከተማ ዛሬ ተሳታፊዎችን ለመምረጥ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሸነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ እንዳሉት፣ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ሲንጸባረቁ ይታያሉ። 

ይህንን ልዩነትና አለመግባባት ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት አገራዊ የህዝብ ምክክሮችን ሁሉን ባሳተፈ አግባብ ለማካሄድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ይሄም አገራዊ መግባባትን በቀጣይ ለመፍጠር እንደሚያስችል ያመለከቱት ዶክተር አይሮሪት፣ በኮሚሽኑ የሚዘጋጁ የህዝብ ምክክሮች አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

በሂደትም በህዝቦች መካከል መተማመንና አብሮነትን በማጠንከር እየተሸረሸሩ ያሉ እሴቶችን ለማደስ የሚያግዙ መሆኑን ተናግረዋል።  

ኮሚሽኑ ዛሬ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣ ማካሄዱን ገልጸው፣ የተሳታፊዎች መረጣ በቀጣይም በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። 

በእዚህ ታሪካዊ ሂደት የክልሉ ህዝብ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩሉን እንዲወጣም ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተሳታፊዎች መረጣ ላይ በክልሉ የተለያዮ የማህበረሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተሳታፊዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል።

የአጀንዳ አሰባሳቢ ተወካዮች መረጣው አካታችነትን፣ ግልጽነትን፣ አሳታፊነትንና ተዓማኒነትን ያገናዘበ እንዲሆን ኮሚሽኑ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው የተወካዮች መረጣ ሰመራ ከተማን ወክለው ከአርብቶ አደር የማህበረሰብ ክፍል የተመረጡት አቶ ኖራ ኢሴ በበኩላቸው እስከገጠር ቀበሌ ድረስ በመሄድ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በሎጊያ ከተማ ወጣቶችን በመወከል የተመረጠው ወጣት መሐመድ ቃሲም በበኩሉ በህብረተሰቡ በተለይም በወጣቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለይቶ ለማውጣት ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጿል።

በተለይ ሀገራዊ ፋይዳና ለህዝቦች አብሮነት ጠቀሜታ ያላቸውን ጉዳዮች በአጀንዳነት እንዲያነሱ የማድረግ ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

ሌላው የተወከለው መምህር ዘሪሁን ታዲዮስ በበኩሉ፣ አገራዊ ምክክሩ ለሰላምና ለሁለንተናዊ እድገት ያለውን ጠቀሜታ በማስረዳት አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በታማኝነት እንደሚወጣ ተናግሯል።

በአፋር ክልል በ48 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ 864 ተሳታፊዎች እንደሚመረጡ ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም