ብዝሃነትን እንደ ፀጋ በመቀበል ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ መስራት ይጠበቅብናል - ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ

ሀዋሳ ፤ ህዳር 22/2016 (ኢዜአ)፡- ብዝሃነትን እንደ ፀጋ በመቀበል ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ገለጹ።

በሲዳማ ክልል 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ክልላዊ ማጠቃለያ መርሃ ግብር በተለያዩ ዝግጅቶች በሀዋሳ ከተማ ተከናውኗል ።


 

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ ብዝሃነትን እንደ ፀጋ መቀበል ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ መሠረት ሲሆን ለህብረብሔራዊነትና ለጋራ ሀገራዊ ራዕይ ግንባታ መሳሪያ መሆኑንም ተናግረዋል።

''ብዝሃነታችንን እንደ ፀጋ በመጠቀም በአንድነትና በወንድማማችነት ኢትዮጵያን  ለማሳደግ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል'' ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዓሉ በክልል ደረጃ ከመጠቃለሉ በፊት በወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ባሉ በተለያዩ አደረጃጀቶችና በትምህርት ቤቶች መከበሩን ጠቅሰዋል ።

በዓሉ በርካታ ማህበረሰብን የሚጠቅሙ በጎ ተግባራት በማከናወን መከበሩን አስታውሰው የደም ልገሳ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ የከተማ ፅዳትና ውበት ሥራ እንዲሁም የማዕድ ማጋራት ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ በቀለ ፍሰሀ፣ ''ከዚህ በፊት ልዩነቶቻችንን እንደ ውበትና አቅም የመመልከት ክፍተቶች ይታዩ ነበር'' ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህብረብሔራዊነት ላይ ያተኮረ የፌዴራል ሥርዓት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ማየታቸውን ጠቅሰዋል ።

ወይዘሮ ምንትዋብ ገብረመስቀል በበኩላቸው ''ብዝሃነታችን ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ አብሮን የኖረ የፈጣሪ  ፀጋ ነው'' ብለዋል ።

''ይህንን ፀጋችንን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ተከባብረንና ተደጋግፈን በመስራት ጠንካራ ሀገር መገንባት ይገባናል'' ነው ያሉት ።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ከፌዴራልና ከአጎራባች ክልሎች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከሲዳማ ክልል፣ ከዞኖች፣ ከወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም