የፌደራል ሥርዓቱ በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፡-የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የፌደራል ሥርዓቱን በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ  ዘሃራ ዑመድ ገለጹ። 

18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል። 


 

በመድረኩ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበር ያለው ጠቀሜታና የፌዴራሊዝም ምንነትና ባህሪያትን የሚዳሰሱ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ  ዘሃራ ዑመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የበዓሉ መከበር ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የመቻቻልና የመከባበር ባህልን ይበልጥ ያዳብራል።

በሕዝቦች መካከል እምቅ ባህላዊ እሴቶች በመገንባትና በፌዴራል ሥርዓቱ የዳበረውን አንድነት ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር ብዝኃነትን በማስተናገድና ሕብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያን በማጠናከር አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

ስለዚህም የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የፌደራል ሥርዓቱን በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።  

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው፤ የበዓሉ መከበር የብሔር፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ማንነቶች ዕውቅና እያገኙ እንዲሄዱ ያስችላል ብለዋል።


 

በዓሉ ማንነቶችን እርስ በእርስ ለማስተዋወቅ እድል ከመስጠቱ ጎን ለጎንም እነዚህን ልዩነቶች በማቻቻል አገራዊ አንድነትን ለማጠናከርም ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ነው የገለጹት።

በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ መህዲም የበዓሉ መከበር አንደኛው የሌላኛውን ባህልና እሴት እንዲያውቅ ያግዛል ብለዋል።

እንዲሁም በህዝቦች መካከል ጠንካራ የሆነ ትስስር በመፍጠር ሕብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አገር መሆኗን በመገንዘብ እርስ በእርስ በመደጋገፍ ችግሮቻችን በጋራ መቅረፍ አለብን ብለዋል።

18ኛው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት «ብዝኃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ኃሳብ በጅግጅጋ ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም