ህፃናት መሰረታዊ መብቶቻቸውና ጥቅማቸው እንዲከበርላቸው ሁሉም መረባረብ አለበት -- ቋሚ ኮሚቴው

አዳማ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ):- ህፃናት መሰረታዊ መብቶቻቸውና ጥቅማቸው እንዲከበርላቸው ሁሉም መረባረብ እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ጤናና ማህበራዊ ልማት ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ''ለዛሬዎቹ ህፃናት  ፍቅርና በጎነትን እናውርስ'' በሚል መሪ ቃል ለ18ኛ ጊዜ የህፃናት ቀን በአዳማ ተከብሯል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀስሙ ማሞ በዚሁ ጊዜ ''ስለ ህፃናት ስናስብ ስለ ነገ የኢትዮጵያ ተስፋ ነው የምናልመው፣ ህፃናትን ፍቅር፣ መቻቻል፣ መተባበርና መተጋገዝ  ማስተማር አለብን'' ብለዋል።

''ቀኑን ስናስብ ከእናቶቻቸው ጋር ጎዳና ላይ የወጡ ህፃናትና ልጆችን ከጎዳና ማንሳትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በመደገፍ ጭምር መሆን ይገባል"' ነው ያሉት።

በተለይ የህፃናት ማህበራዊ ደህንነት እንዲረጋገጥ፣ መሰረታዊ መብቶቻቸውና ጥቅማቸው እንዲከበር ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላቶች በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ዑሞድ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የህፃናት መሰረታዊ መብቶችና ጥቅሞች እንዲረጋገጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን መደገፍና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የህፃናት እንክብካቤና አስተዳደግ ላይ የቤተሰብ ግንዛቤ እንዲጎለብት የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተው ህፃናትና ልጆች ላይ የሚሰራው ስራ ሀገርና ትውልድን ከማነፅ አንፃር የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህፃናት ፓርላማ አፈጉባኤ ታዳጊ ቅዱስ ሞላ በበኩሉ የህፃናት መብትና ጥቅሞች እንዲከበሩ እንዲሁም ማህበራዊ ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተባብረው መስራት አለባቸው ብሏል።


 

 በተለያየ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሚገኙና ወደ ጎዳና የወጡ ህፃናትና ልጆች የመደገፍ ስራ ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባም አስረድቷል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም