ቀጥታ፡

በቄለም ወለጋ ዞን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ  በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

ጊምቢ ፤ ህዳር 22/2016  (ኢዜአ)፡- በቄለም ወለጋ ዞን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

የቄለም ወለጋ ዞን ዋና አስተዳደሪና በዞኑ የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ገመቹ ጉርሜሳ እንደገለጹት የዞኑ ህዝብ የግድቡ ግንባታ መሰረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ የተለያየ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የአካባቢውን ሰላም እየጠበቀ በልማት ስራም በሚችለው አቅም እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታም ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ 


 

በዘንድሮ ዓመትም በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች ለሶስት ሳምንት በተደረገ የንቅናቄ መርሃ ግብር በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ13 ሚሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ገቢው የተሰበሰበው ከጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ህዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑን የገለጹት አቶ ገመቹ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ17 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው እቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ነዋሪዎች የግድቡ ግንባታ እሰኪሚጠናቅቅ ድረስ የጀመሩትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ አቶ ገመቹ ጠይቀዋል።

ከዞኑ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሳምሶን እምሩ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለያየ መልኩ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ግድቡ የህዝቡ በመሆኑ በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረው፤ የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

''ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጰያ ልጆች ላብ እየተሰራ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው'' ያሉት ደግሞ  የዞኑ ነዋሪ አቶ  ጫላ ኢንሰርሙ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ አሁንም እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም