ቀጥታ፡

ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር በመንግስት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል- ፌዴሬሽኑ

አሶሳ፣ ህዳር 22 /2016(ኢዜአ)፡-ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር በመንግስት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን አስታወቀ። 

31ኛው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በአሶሳ ከተማ እየተከበረ ነው።


 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ሁሉም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። 

አካል ጉዳተኞችን በተሻለ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጠቃለለ ህግ ሲዘጋጅ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አባይነህ፣ ህጉ ሲጸድቅ አካል ጉዳተኞችን በሁሉም መስክ በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የተጠቃለለ ህጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፈጥኖ እንዲጸድቅም ጠይቀዋል።  

"እየተተገበሩ ካሉ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚነኩ ናቸው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀሪ ዓመታት ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሪት አዳነች አስራት በበኩላቸው፣ አካል ጉዳተኞች የማይችሉት ጉዳይ ስለሌለ በሁሉም መስክ ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።  


 

"በተለይ በአገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ለማጠናከር በየዘርፉ የሚያጋጥሟቸው እንቅፋቶች ተባብሮ ማስወገድ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።

"በመድረኩ የሚነሱትን ጨምሮ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጡ ህጎችን ተፈጻሚነት ማጠናከር የቢሮው የቀጣይ ትኩረት ነው" ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ እናትነሽ ማሩ ናቸው።


 

በዓለም ለ32ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ31ኛ ጊዜ በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ከሁሉም ክልሎች የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አመራሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም