በ2024 በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የውሃ ዋና ሻምፒዮናና በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚደረገው ኦሊምፒክ የሚወዳደሩ ዋናተኞች ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
በ2024 በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የውሃ ዋና ሻምፒዮናና በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚደረገው ኦሊምፒክ የሚወዳደሩ ዋናተኞች ተለዩ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፡- በ2024 በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የውሃ ዋና ሻምፒዮናና በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚደረገው ኦሊምፒክ በወንዶች በረከት ደምሴ በሴቶች ደግሞ ሊና ዓለማየሁ ተመረጡ።
የኢትዮጵያ የውሃ ዋና ስፖርት ተሳትፎ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2012 በተከናወነው በለንደን ኦሊምፒክ የሚጀምር ሲሆን፤ በወቅቱ በሴቶች ያኔት ስዩም በወንዶች ደግሞ ሙሉዓለም ግርማ በ50 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ ከለንደን ኦሊምፒክ ጀምሮ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 እስከተካሄደው የጃፓን ቶኪዮ ኦሊምፒክ ድረስ በውሃ ዋና በሦስት ኦሊምፒኮች እንደተሳተፈች የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ዘንድሮም ፌዴሬሽኑ በ2024 በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የውሃ ዋና ሻምፒዮና እና በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚደረገው ኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ በጊዮን ሆቴል ውድድር አካሂዷል።
በዚህም ውድድር በሁለቱም ፆታ በነፃ ቀዘፋ እና በቢራቢሮ ውድድሮች ተካሂደው፤ በወንዶች በረከት ደምሴ ከአዲስ አበባ በሴቶች ሊና ዓለማየሁ ከኦሮሚያ አንደኛ ሆነው ተመርጠዋል።
የተመረጡ አሸናፊ አትሌቶች በቂ ዝግጅት አድርገው ኢትዮጵያን በመወከል በዶሃ የዓለም ውሃ ስፖርቶች ውድድርና በፓሪስ ኦሊምፒክ እንደሚሳተፉ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት መሠረት ደምስ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የውሃ ዋና ተወዳዳሪዎቹ ስለተለዩ በቀጣይ የአሰልጣኝ ምርጫ ተካሂዶ ዋናተኞቹ ይሰለጥናሉ።
የተመረጡት ዋናተኞችም በየካቲት ወር በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የውሃ ዋና ሻምፒዮና የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሚወስነው መሠረት አዲስ አበባ ወይም ቢሾፍቱ ላይ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚደረገው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድርም ዋናተኞቹ የሚያደርጉትን ዝግጅት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ልምምድ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 በፈረንሳይ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር እስካሁን በአትሌቲክስና በውሃ ዋና መሳተፏን እንዳረጋገጠች ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።