ስልጠናው አንድነቷ የተጠበቀና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት አቅም የፈጠረ ነው-የስልጠናው ተሳታፊዎች

ባህር ዳር፤ ህዳር 22/2016 (ኢዜአ)፦ ለመንግስት አመራር አባላት እየተሰጠ ያለውን ስልጠና እየተከታተሉ ያሉ ሰልጣኞች ስልጠናው አንድነቷ የተጠበቀና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት አቅም የፈጠረ መሆኑን የስልጠናው ተሳታፊዎች ገለጹ።

በባህር ዳር የስልጠና ማዕከል “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተሰጠ የሚገኘው 4ኛ ዙር የመንግስት አመራሮች ስልጠና ቀጥሏል።


 

የስልጠናው ተሳታፊ ወይዘሮ አስረሳሽ ኩምሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ችግር ለመውጣት የአመራሩ አቅም ግንባታ ስልጠና ለውጥ የሚያመጣ ነው። 

''ስልጠናው ገዥና የወል ትርክቶች ላይ አተኩሮ በመስራት አገራችንን ወደ ብልጽግና ጉዞ ማሻገር የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነው '' ብለዋል።

እንዲሁም ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን አጠናክሮ በማስቀጠል በህብረ ብሄራዊ አንድነት ኢትዮጵያን ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ አቶ ደጀኔ ጤና በበኩላቸው፤ ስልጠናው ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ አመራሮች በአንድ ስፍራ እውቀትና ክህሎትን የሚገበያዩበት በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል። 


 

ይህም የህዝቡን አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳትና መደጋገፍ በማስቀጠል አገሪቷ የገጠሟትን ችግሮች በጋራ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። 

በእያንዳንዱ ክልል ያለው ችግር ሁሉም አመራር እንዲረዳው በማድረግ በቀጣይ በጋራ በመቆም መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እየተገነባበት ያለ ስልጠና መሆኑን አስረድተዋል።   

በተጨማሪም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አመራሮች ልምድና ተሞክሮ ለመቀያየር እድል የሰጠ በመሆኑ በቀጣይ መጠናከር ያለበት ጉዳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።


 

"በስልጠናው ዘላቂ ተጠቃሚነትንና የአገር አንድነትን እንዴት አጠናክረን ማስቀጠል አለብን የሚል ግንዛቤ ያገኘሁበት ነው" ያሉት ደግሞ አቶ አብርሃም አምቾ ናቸው።

''በተለይም በአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ላይ የተሰጠው ስልጠና ግብርናን፣ ጤናን፣ ፋይናንስን፣ ገቢ መሰብሰብንና ሌሎች የኢኮኖሚ ልማት ስራዎችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማሳለጥ እንደሚገባ እውቀት የያዝንበት ነው'' ብለዋል።

በተጨማሪም የመንግስትን አሰራር በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ሙስናን እንዴት መከላከል እንደሚቻልና ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አቅም የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በባህር ዳር የስልጠና ማዕከል ''ከእዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ሀሳብ ከአንደኛ እስከ 3ኛ ዙር  ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም