ቀጥታ፡

በክልሉ የተጀመረው የሙስናና ብልሹ አሰራር የመታገል ስራ እንደሚጠናከር ተገለጸ

ሆሳዕና፤ ህዳር 22/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመረው የሙስናና ብልሹ አሰራር የመታገል ስራ እንደሚጠናከር የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል "ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በጋራ እንታገለዉ" በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እየተከበረ ነው ።

በዚሁ ጊዜ የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ማሞ ቴጋ እንዳሉት በክልሉ የተጀመረው ሙስናና ብልሹ አሰራር የመታገል ስራ ይጠናከራል።

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራር ለዘላቂ ልማት መሰናክል ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በየደረጃው እየተደረጉ ያሉ የንቅናቄ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።

በተለይም በዘርፉ የሚስተዋለው ተለዋዋጭ የሆነ ብልሹ አስራር አካሄድን ለመታገል ከሰው ኃይል ማደራጀት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል ።

የክልሉ መንግስት ሙስናን በጋራ በመታገል የህዝቡን የእድገትና የልማት ፍላጎትን በአጠረ ጊዜ ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በክልሉ በመሬት፣ በግዥ፣ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ፣ ከግንባታና ኮንትራት አስተዳደርና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመግታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በዞኑ የሙስናና ብልሹ አሰራርን በመታገል የሚፈጠሩ ብክነቶች ለማስቀረት የተቀናጀ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻር ግብረ ገብነት ላይ መሰራት እንዳለበት አንስተው መምህራንና የሀይማኖት ተቋማትም በስነ-ምግባር የታነፁ ዜጎችን በማፍራት ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰውና የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም