የኦሞ ወንዝን ከጎርፍ ስጋትነት ወደ ሀብት ለመቀየር እየተሰራ ነው---ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሞ ወንዝን ከጎርፍ ስጋትነት ወደ ሀብት ለመቀየር እየተሰራ ነው---ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ጂንካ ፤ ህዳር 22/2016 (ኢዜአ)፡-የኦሞ ወንዝን ለልማት በማዋል ከጎርፍ ስጋትነት ወደ ሀብት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት በአካባቢው ነዋሪዎችና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ዛሬ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን ከጎርፍ ተጎጂዎች ጋርም ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የጎርፍ ተጎጂዎቹ ወንዙ በየዓመቱ ባልታሰበ ጊዜ ሞልቶ በመፍሰስ ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በእዚህም በብዙ ጥረት ያፈሩትን ቤትና ንብረት ከመውደሙና ከመፈናቀላቸው ባለፈ ከብቶቻቸውን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረገባቸው መሆኑን አንስተዋል።
በጎርፉ ጉዳት ላይ ከተጎጂዎች ጋር የመከሩት ርዕሰ መስተደድሩ አቶ ጥላሁን በበኩላቸው እንዳሉት፣ የኦሞ ወንዝ በየዓመቱ በአርብቶ አደሮች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ወደተግባር ሥራ ገብቷል።
በአሁኑ ወቅትም ወንዙ በየዓመቱ የሚያደርሰውን አደጋ መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን ነው የገለጹት።
በዚህም ወንዙን ለግብርና ልማት በማዋል ከስጋትነት ወደ ሀብትነት በመቀየር በተፋሰሱ አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ኑሮ ለመለወጥ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ ከሚሰሩ ተግባራትም በኦሞ ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ አርብቶ አደሮችን ከስጋት ነፃ ወደሆኑ አካባቢዎች ማስፈር አንዱ መሆኑንና ለእዚህም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።
አዲስ በሚቋቋሙ መንደሮችም አርብቶ አደሮቹ መስኖ ተጠቅመው ሰብል፣ የእንስሳት መኖ እና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ይደረጋል ብለዋል።
ለአርብቶ አደሮቹ የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት የሚያስችል የተቀናጀ ዕቅድ ተነድፎ ወደተግባር መገባቱንም አቶ ጥላሁን አመላክተዋል።
በአካባቢው ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝና በቂ የሰው ሀይል እንዳለ የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ እነዚህን በመጠቀም አርብቶ አደሮቹን ከችግሩ ለማውጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በአሁኑ ሰአት የክልሉ መንግስት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆኑን የዕለት ደራሽ ምግቦችን እና ሌሎች ቁሶችን ለተጎጂዎች እያቀረበ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተጎጂዎቹ ለወባ እና ለውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይጋለጡ ከተላላፊ በሽታዎች የመጠበቅ ሥራ ጎን ለጎን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በጎርፍ ተጎጂዎች ምልከታና በውይይቱ ላይ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ ሌሎች የክልሉ ሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።