ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቡና ንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ትፈልጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቡና ንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ትፈልጋለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፡- ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቡና ንግድ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ የቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዱ ጂሃኦ ገለጹ።
በቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶና ሌሎች የምክር ቤት አባላት ገላን የሚገኘውን ኤ ኤም ጂ ቡና ላኪ ድርጅትን ጎብኝተዋል።
የፓርቲው አባላት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
የቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዱ ጂሃኦ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ገበያ በስፋት እየታወቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የቻይና ባለሃብቶች በቡና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በኢትዮጵያ መኖሩን መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱና የኢትዮጵያ ቡና በብዛት እና በጥራት ተመርቶ በስፋት ለዓለም ገበያ መቅረብ እንዲችል የበኩላቸውን ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት ቡናን በጥራትና በብዛት ማቅረብ ከቻለች የገበያ ዕድሉ በቻይና መኖሩን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በቻይና ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ቀደም ብሎ የነበረውን ሻይ የመጠጣት ባህሉን ወደ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም የተረዱ የቻይና የቡና ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና እየገዙና የንግድ ትስስር እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ይህንም ለማጠናከር ቋሚ ከሚቴው ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመቀራረብ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን ቡና በጥራትና በብዛት በማምረት ከምትልክባቸው ቀዳሚ ሀገራት ውስጥ ቻይና አንዷ መሆኗን ገልፀዋል።
ለአብነትም ወደ ቻይና በ2015 ዓ.ም 10 ሺህ 879 ቶን ቡና ተልኮ 70 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ በዘንድሮው ሩብ ዓመት 2 ሺህ 285 ቶን ቡና የተላከ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በጥራትና በብዛት እያመረተች መሆኑን አስረድተው፤ የቡና ገበያ በቻይና እንዲሰፋ ጠይቀዋል።
እንደዚሁም የቻይና ባለሃብቶች በቡና ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ መሰማራት መጀመራቸውን ገልጸው፤ ይህን ተግባራቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።