የጅማ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ጽዱ እና ማራኪ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ጽዱ እና ማራኪ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው

ጅማ፣ ህዳር 22 /2016(ኢዜአ):- የጅማ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ጽዱ እና ማራኪ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለጸ።
በጅማ ከተማ የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች፣ መዝናኛ ፓርኮች እና የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገዶች እየተገነቡ ነው።
ባለፋት ሶስት አመታት ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ጽዱ እና ማራኪ አካባቢ ለመፍጠር የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጅማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅና የጽዳትና ውበት የስራ ሂደት መሪ ወይዘሮ ፈትያ መሀመድ ገልጸዋል።
በተለይም ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈው የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ በ12 ሄክታር መሬት ላይ "ሸንኮሪ" የተሰኘ ፓርክ ጨምሮ የተለያዩ የጽዳትና ውበት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በጅማ ከተማ በሶስት ዙር የተገነባው የአዌቱ ወንዝ ዳርቻ ልማት እና የተገነቡ የተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎች ለከተማዋ ልዩ ውበት ያጎናጸፉ፣ የስራ እድል የፈጠሩ እና ጽዱ አካባቢ ማድረግ የቻለ ነው ብለዋል።
በሁለት አመት ለመገንባት ከታቀደው አምስት ኪሎሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ 2 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትሩ ባለፈው አመት፣የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው የአስፋልት መንገድ ደግሞ በዚህ አመት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጅማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢስማኤል ሱሌማን በበኩላቸው በከተማዋ የተሰራው የልማት ስራ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ከተማዋ በእንግዶች ተወዳጅ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።
በከተማዋ የተገነቡት ፓርኮች፣ መዝናኛዎችን እና የአረንጓዴ አካባቢዎችም ሆኑ መንገዶች ለቱሪዝም ገቢ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
ውብና ጽዱ አካባቢ የመፍጠር ስራው ከተማዋን እንግዶች ለመዝናናት እና ለመጎብኘት የሚመርጧት ከዚያም ባለፈ ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው የተሰሩት መንገዶችና የመዝናኛ ቦታዎች የከተማዋን ውበትና ንጽህና የጠበቁ በመሆናቸው ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል።
የጅማ ከተማ ነዋሪው አቶ ተማም አህመድ፣ ''በከተማዋ የሚሰሩ መንገዶችና የጎርፍ ማሳለፊያ ቦዮች የነበረብንን ችግር ቀርፎልናል፣ ንጹህና ውብ ከተማ ተፈጥሯል ''ብለዋል።
በወንዞች ዳርቻ የተሰሩ መዝናኛዎችም ከዚህ በፊት ለማየትም ሆነ በዚያ አካባቢ ለማለፍ የሚያስችግሩ አካባቢዎችን በማጽዳት ውብ ማረፊያ እና መዝናኛ ስፍራን መፍጠር ያስቻለ ነው ብለዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ከዲጃ አወልም እንዲሁ በከተማዋ የመንገድ ጥበትና እጥረት ስለነበር ለመንቀሳቀስ አስቻጋሪ የነበረው ሁኔታ ተቀይሮ አሁን የተሰሩ መንገዶች ሰፊና ለመንቀሳቀስ ምቹ መሆናቸው ተናግረዋል።
''በቀጣይም የከተማችንን የመንገድ እና የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን የበለጠ በማስፋፋት ጅማ ከዚህ የተሻለ ምቹና ውብ እንድትሆን መስራት ይጠበቅብናል'' ብለዋል።