ቀጥታ፡

የከተሞች መዋቅራዊ ፕላን የቀጣዩን ትውልድ የተሻለ መዳረሻ መሠረት ማድረግ ይኖርበታል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ) የከተሞች መዋቅራዊ ፕላን የቀጣዩን ትውልድ የተሻለ መዳረሻን መሠረት ማድረግ እንደሚኖርበት በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ-ልማት  ቢሮ  ኃላፊ  አህመዲን ሙሀመድ ገለጹ።

የደብረ ብርሃን ሪጂኦ-ፖሊታን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ሂደትና የስማርት ሲቲ ጽንሰ ሃሳብ ላይ  በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 


 

በመድረኩ በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማና መሠረተ-ልማት  ቢሮ ኃላፊ አህመዲን ሙሀመድ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ  ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን  ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ-ልማት  ቢሮ ኃላፊ አህመዲን ሙሀመድ፤ ከተሜነትን በውጤታማና ተሻጋሪ መዋቅራዊ ፕላን መመራት አለበት።

ይህ መሆን ካልቻለ ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። 

የከተሞችን የመሠረተ-ልማት ተደራሽነት ለማስፋትና የአደጋ ተጋላጭነት ምላሽ ለመስጠት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በቴክኖሎጂ የታገዘ ስማርት ሲቲ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። 

ደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪና የዕውቀት ማዕከል በመሆኗ የስማርት ሲቲ መዋቅራዊ ፕላን እንዲኖራት የተደረገውን ሥራ አድንቀው፤ የከተሞች መዋቅራዊ ፕላን የቀጣዩን ትውልድ የተሻለ መዳረሻ ታሳቢ ማድረግ እንደሚኖርበት አንስተዋል። 


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ  ከንቲባ በድሉ ውብሸት፤ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ሶስት ዓመታት የከተማዋን የስማርት ሲቲ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል። 

ደብረ ብርሃን ከተማ የዕድገት ምሳሌ እየሆነች የመጣች ከተማ በመሆኗ ስፋትና ዕድገቷን የሚመጥን የዘመናዊ ስማርት ሲቲ ግንባታ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማን ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት ለነዋሪዎቿ  ምቹ፣ ተመራጭና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል የስማርት ሲቲ ግንባታ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 


 

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ዕድገትና ስፋት እያሳዩ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ደብረ ብርሃን አንዷ መሆኗን ተናግረዋል። 

ከተማዋ እያስመዘገበች በምትገኘው ዕድገትና ስፋት ልክ ዘመኑ የደረሰበትን መዋቅራዊ የስማርት ሲቲ ግንባታ መዋቅራዊ ፕላን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል። 

ለዚህም የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የከተማዋን ታሪካዊ ቀደምትነት፣ አሁናዊነትና የቀጣይ መዳረሻን ታሳቢ ያደረገ መዋቅራዊ የስማርት ሲቲ ግንባታ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል። 

የደብረ ብርሃን ከተማ እድገት እያስመዘገበች የምትገኝና ረዥም ዓመታትን የተሻገረ ታሪክ ያላት ከተማ መሆኗም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም