ቀጥታ፡

ማዕከሉ በ215 ሚሊዮን ብር ወጪ ገበያ የሚያረጋጉ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው

ሀዋሳ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)-የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሀዋሳ የፍጆታ እቃዎች ሽያጭ ማዕከል ገበያን ለማረጋጋት በ215 ሚሊዮን ብር ወጪ የፍጆታ ምርቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን አስታወቀ ።

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመዴ ገረሱ ለኢዜአ እንዳሉት ማዕከሉ በተያዘው ዓመት 215 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 30 የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችን ለሃዋሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች እያቀረበ ነው።

ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ካሉ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች መካከል የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ የቤትና የግል ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።


 

የሽያጭ ማዕከሉ የተወሰነ ትርፍን ብቻ ያገናዘበ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘመዴ፣ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት አሰራርን ብቻ መከተሉም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ በሽያጭ ማዕከሉ ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን የፍጆታ እቃዎች ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ከጥሬ እቃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ባጋጠመ ተግዳሮት በሩብ በጀት ዓመቱ ለማከናወን የተያዘውን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት አልተቻለም ብለዋል ።

አቶ ዘመዴ እንዳሉት በመንግሥት ድጎማ ለሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተፈቀደው ከ96 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይትን ጨምሮ ሌሎች የፍጆታ ምርቶች በማዕከሉ በኩል ተሰራጭተዋል።

በእዚህም የህብረተሰቡን ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ለማጣጣም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥትና የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞችና የሸማች ማህበራትን በማበረታታት የፍጆታ እቃዎችን በቀጥታ እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። 

ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቱ የንግድ ግብይት ሥርዓት የተረጋጋ፣ ዘመናዊ፣ አስተማማኝና ውጤታማ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አቶ ዘመዴ አመልክተዋል።

ለዚህ እውን መሆን በየደረጃው ያለው የንግዱ ማህበረሰብ ዘመናዊ የንግድ አሰራር እንዲከተልና ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገር ኮርፕሬሽኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል የደብረወርቅ ቀበሌ ሸማቾች መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበር አንዱ ነው።

የማህበሩ ተወካይ አቶ የትራ አቃሞ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ላይ  የሚታየውን እጥረት ለመፍታት ኮርፖሬሽኑ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ማህበሩ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ማዕከሉ ከኮርፖሬሽኑ በሚያገኘው ዕቃ አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ማህበሩ ከማዕከሉ ከሚያገኘው ዕገዛ በተጨማሪ ከአምራች አርሶ አደሩ ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የእህል ምርቶችን ለአባላቱ ለማሰራጨት ማቀዱን ጠቁመዋል።

 ከደብረወርቅ ቀበሌው ነዋሪዎች መካከል አቶ አያሌው ፋንታ አንዳሉት ማህበሩ ከማዕከሉ የሚወስደውን የፍጆታ እቃዎች ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች የሚያገኛቸውን ሸቀጦች ለህብረተሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚህም እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ መሆኑን ነው የገለጹት።


 

አቶ አያሌው እንዳሉት በአዘቦት ቀናትና በበዓላት ወቅት በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ የፍጆታ ምርቶች ለህብረተሰቡ በፍትሀዊነት እየቀረቡ ናቸው።

በመንግስት ድጎማ እየቀረቡ ያሉ የፍጆታ እና የእህል ምርቶች ሸማቹ ማህበረሰብ በሚፈልገው መጠን ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ እንዲመቻችም አቶ አያሌው ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም