ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ እና አቶ ታደሰ ለማ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕጩ ሰብሳቢ ሆነው ቀረቡ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፦ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ እና አቶ ታደሠ ለማ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ዕጩ ሆነው ቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስምንት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ መልማይ ኮሚቴ መሰየማቸው ይታወሳል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለን ጨምሮ የኮሚቴው አባላት በተገኙበት የእስካሁን ክንውኖቹን አስመልክቶ ኮሚቴው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። 

ኮሚቴው ባደረገው የጥቆማ መቀበል ሂደት ከደረሱት 52 ወንዶች፣ 4 ሴቶች በድምሩ 56 ሰዎች ጥቆማዎች መካከል በሶስት ደረጃዎች የማጣራት ሂደት ለመጨረሻ ዙር አምስት ዕጩዎች መለየታቸው ተገልጿል።

ከ5ቱ መካከልም ኮሚቴው በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት ሁለቱን ለመጨረሻ ዙር ለይቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዲቀርቡ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን አስታውቋል።

በዚህም ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ አበባው እና አቶ ታደሠ ለማ ገርቢ መስፈርቱን አሟልተው መለየታቸውን ኮሚቴው ገልጿል።

በኢትዮጵያ ነጻ፣ ፍትሃዊና ታአማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ይረዳ ዘንድ የዕጩ ሰብሳቢ ልየታ ሂደቱ ብርቱ ጥንቃቄ የተደረገበት እና ኮሚቴው ቀን ከሌሊት በትኩረት የሰራበት ስለመሆኑም ተገልጿል።

የስነ-ምግባር እና የፖለቲካ ተሳትፎ ገለልተኝነት ከምልመላ መስፈርቶች መካከል እንደሆኑ ኮሚቴው አብራርቷል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ሁለቱ ዕጩዎች መካከል አንድ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ በፓርላማ ቀርቦ የሚሾም ይሆናል።

በመግለጫ ላይ እንደተጠቆመው በትምህርት ደረጃ ረገድ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሰላምና ደህንነት ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በህዝብ አስተዳደር ተጨማሪ ማስተርስ ዲግሪ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል።

በስራ ልምድ ረገድ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ለስምንት ዓመታት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፅህፈት ቤት ሃላፊነት ሆነው  ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።

በተመሳሳይ አቶ ታደሠ ለማ የመጀመሪያ ዲግሪ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው ተገልጿል።

አቶ ታደሰ ካላቸው ልምድ መካከል በምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ምርጫ ክልል ሃላፊ ሆነው መምራታቸው ተወስቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም