የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፡-  ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

''ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አስተባባሪነት ከተማ አቀፍ የማጠቃለያ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ  ዘሃራ ዑመድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ  ዘሃራ ዑመድ እንዳሉት፤ የበዓሉ መከበር ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሊኖራቸው የሚገባው የመቻቻልና  የመከባበር ባህልን ይበልጥ ያዳብራል።

በሕዝቦች እምቅ ባህላዊ እሴቶች እየተገነባና በፌዴራል ሥርዓቱ የዳበረውን አንድነት ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው፤ የበዓሉ መከበር የአገሪቱ ውበት የሆኑ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የባህል እንዲሁም የሃይማኖት ማንነቶች መኖራቸው ዕውቅና እያገኘ እንዲሄድ አድርጓል ነው ያሉት።

እነዚህን ልዩነቶች በማቻቻልና አንድነትን በማጠናከር ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙኃኑ የሚስማማበት አስተሳሰብ እየሆነ እንዲመጣ አስችሏል ብለዋል፡፡

የበዓሉ መከበር በመፈቃቀድ ታላቋን ኢትዮጵያ የገነቡትን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከውብ ባህላቸው ለመተዋወቅ እና ለልዩ ልዩ  ማንነቶች ዕውቅና በመስጠት፣ የመገለልና የመጨቆን ስሜቶችን በማስወገድ አገራዊ አንድነትን ያጠናክራል ብለዋል።

18ኛው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን   በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት «ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ  ይከበራል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም