በምዕራብ ሀረርጌ ዞን 59 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን 59 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር እየለማ ነው
ጭሮ፤ህዳር 22 /2016(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሀረርጌ ዞን 59 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የስንዴ ምርጥ ዘር በበጋ መስኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቡሽራ አደም እንደተናገሩት በምዕራብ ሀረርጌ ዞን 59 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ምርጥ ዘር ልማት እየተካሄደ ነው።
በዞኑ የበጋ መስኖ ስራው ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸው እስከ አሁን ባለው ጊዜ 40 ሺህ ሔክታር መሬት በስንዴ ምርጥ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
በዞኑ 15ቱም ወረዳዎች አርሶ አደሩ እንደ የወረዳዎቹ የአየር ንብረት ሁኔታ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያካሄደ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ከህብረት ስራ ዩኒየኖችና ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ከልማቱ የተሻለ ምርት ለማግኘት እንዲቻል የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እንዲያጠናክሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ሰብሉ በበሽታ እንዳይጠቃም ባለሙያው ተከታታይነት ያለው ምልከታ በማድረግ ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንዲችል ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልጸዋል።
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ ከታቀደው 7 ሺህ ሔክታር ውስጥ 4 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በስንዴ ምርጥ ዘር የመሸፈን ስራ እየተከናወነ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ አህመድ ገልፀዋል፡፡
ጉምቢ ቦርደዴ ከዞኑ ውሃ አጠር ወረዳዎች አንዱ እንደ መሆኑ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የስንዴ ምርጥ ዘር ዝርያዎችን በማግኘታቸው የአካባቢውን አየር ንብረት መሰረት ያደረገና አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርሶ አደር ለማሸጋገር የሚሰራውን ስራ ምቹ አድርጎታል ሲሉም አስተዳዳሪው አክለዋል፡፡
የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በበጋ መስኖ ልማት በመሳተፋቸው ህይወታቸው ላይ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገልጸው ስራውን በስፋት እያከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ከ3 አመት ወዲህ የጀመሩት አርሶ አደር ሁሴን ቦሩ፣ የበጋ መስኖ በአካባቢያቸው አዲስ መሆኑን ገልጸው ስራው ለዘመናዊ የግብርና ቴክሎጂዎችም ቅርብ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ስንዴን በመስመር መዝራትና ኮምባይነር የመሳሰሉ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጊዜያቸውን በመቆጠብ ምርትም እንዳይባክን የረዳቸው መሆኑን አክለዋል፡፡
አርሶ አደር አብደላ የሱፍም እንዲሁ በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚደረግላቸው ምክርና ክትትልም ምርታማነት ላይ ማተኮርና ከብክነትና አደጋዎች እንዲጠበቁ እንደረዳቸው ጠቁመዋል፡፡
በመንግስት በኩልም በአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል እስካሁን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር መሸፈኑን በክልሉ ግብርና ቢሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ኢንሼቲቭ አስተባባሪ አቶ ጣሃ ሙሜ የገለጹ ሲሆን በክልሉ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማም ተናግረዋል።