በመከላከያ ሠራዊቱና በህዝቡ ቅንጅት አንፃራዊ ሠላም ማምጣት ተችሏል- ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ

170

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2016(ኢዜአ)፦መከላከያ ሠራዊቱ እና ህዝቡ ተቀናጅተው በመሥራታቸው በአካባቢው አንፃራዊ ሠላም ማምጣት ተችሏል ሲሉ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥና የማዕከላዊ ሸዋ ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ገለጹ።

በከሚሴ ከተማ በአካባቢው ፀጥታና ሰላም ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡


 

ሌተናል ጀነራል ሹማ ከአፋር ክልል ዞኖች፣ ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ከተወጣጡ የዞን፣ የከተማ፣ የወረዳና ቀበሌ አስተዳደሮች እንዲሁም ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ሌተናል ጀነራል ሹማ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ እና ህዝቡ ተቀናጅተው በመስራታቸው በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈን መቻሉን ገልፀው፤ ያለጠንካራ አንድነት ጠንካራ ሀገር አይኖርምና ለጋራ አላማ በጋራ በመሰለፍ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚጠበቅብንን መወጣት አለብን ብለዋል።


 

የዞን አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው መከላከያ ሠራዊት ሀገርን ለማሻጋር ዋጋ እየከፈለ እንዳለው ሁሉ እኛም ከጎኑ ሆነን የሚጠበቅብንን በመወጣት ኢትዮጵያን በጋራ እንጠብቃታለን ሲሉ ተናግረዋል።

የረከሰ አስተሳሰብ ይዘው ህዝብ ውስጥ በመመሸግ በደም ለመነገድ የሚጥሩ ፅንፈኛ ሃይሎችን ተከታትለን ለህግ በማቅረብ የመከላከያ ሠራዊቱ እና የፀጥታ ሃይሉ አጋዥ ሆነን እንቀጥላለንም ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአከባቢው ህብረተሰብ ከጥንት ጀምሮ በጋብቻ፣ በባህል፣ በእምነት ተጋምዶ በሀዘንና በደስታ አብሮ የኖረ አሁንም አብሮ ያለ መሆኑን ገልፀው እኔ አውቅልሃለው ባይ ህገ ወጦች የፈጠሩትን ችግር እንደሚያወግዙ እና ከሠራዊቱ ጋር እንደሚሠሩ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም