የሲቪክ ማኅበራት በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ያላቸው ሚና ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016(ኢዜአ)፦ የሲቪክ ማኅበራት በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት የውይይትና የምክክር መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ። 

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር "የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ የባለድርሻ አካላት ሚና" በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል።


 

በውይይት መድረኩ የሲቪክ ማኅበራትና ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ የዳበረ ዴሞክራሲን ለመገንባት በውይይትና በምክክር ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያለመ ነው።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዴሞክራሲ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ ሃላፊ ሞገስ ባልቻ  እንደገለጹት የሲቪክ ማኅበራት በዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸው ጉልህ ሚና ከፍተኛ ነው።

ሲቪክ ማኅበራት በዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል ግንባታ ድርሻቸውን ማበርከት የሚችሉት በጋራ ምክክርና ውይይት የሃሳብ ገበያ ሲፈጥሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የሲቪክ ማኅበራትና ባለድርሻ አካላት ዴሞክራሲው እንዲያብብ ሰላማዊ የሃሳብ ትግልን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ ተጀምሮ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በተቋማት ግንባታና በማኅበረሰብ የአስተሳሰብ ለውጥ ሲረጋገጥ ነው ብለዋል።

ዴሞክራሲ መሠረት የሚይዘው አስተማማኝና ጠንካራ በሆኑ ዴሞክራሲን የሚያለመልሙ ተቋማት ሲዘረጉና ሲገነቡ መሆኑንም አውስተዋል።

የዴሞክራሲ ግንባታ በተቋማት እንቅስቃሴ ጭምር የሚሳካ በመሆኑ ይህም እውን ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የሲቪክ ማኅበራት በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ያላቸው ሚና እንዲጎላ የውይይትና የምክክር መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ የኋላሸት በቀለ በበኩላቸው  ዴሞክራሲው እንዲጎለብት ውይይቱና ምክክሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲጎለብት አካታችነት ባለው መልኩ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። 

የውይይት መድረክ ተሳታፊዎችም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት የተጀመረው ውይይት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም