በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በኢትዮጵያ የተሰራው የአረንጓዴ ልማት በልዩነት የሚታይና አስገራሚ ነው - ቶኒ ብሌር - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በኢትዮጵያ የተሰራው የአረንጓዴ ልማት በልዩነት የሚታይና አስገራሚ ነው - ቶኒ ብሌር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በኢትዮጵያ የተሰራው የአረንጓዴ ልማት በልዩነት የሚታይና አስገራሚ ነው ሲሉ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ገለጹ።
የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር በኮፕ 28 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረትና ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳየውን አውደ ርዕይን ጎብኝተዋል።
አውደ ርዕዩን ከጎበኙ በኋላም አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው ለውጥ ለማሰብ የሚከብድ ነውም ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ካለው ከፍተኛ እመርታ ባሻገር በአረንጓዴ አሻራ ልማትም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል ከፍተኛ ስራ ሰርታለች ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህም ቀደም ሲል ከውጭ ታስገባቸው የነበሩ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች ላይ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ወደ ውጭ መላክ የቻለችበትን ስኬት አስመዝግባለች ነው ያሉት።
ቶኒ ብሌር አክለውም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ የሰራችው አመርቂ ስራ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በልዩነት የሚታይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኮፕ 28 ጉባኤ ላይ ይዛ የቀረበችው አውደ ርዕይም በውጭ ያሉ ማህበረሰቦች የኢትዮጵያ መንግስት በአረንጓዴ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ምን አይነት አስደናቂ ስራ እየሰራ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።