የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መስተጋብር እሴቶች እንዲጎለብቱ መሥራት ይገባናል-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ 

ሐረር፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የአዎንታዊ መስተጋብር እሴቶች እንዲጎለብቱ መሥራት ይገባናል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ።

በሐረር ከተማ 18ኛው የኢትዮጵያ  ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በድምቀት ተከብሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኢትዮጵያ የብዝሃነት አገር መሆኗን በተጨባጭ የሚያሳይ  ነው።''

በዓሉ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ያላቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድነታቸውን ያጠናከሩበት መሆኑንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ያስታወቁት።

አቶ ኦርዲን እንዳሉት የክልሉ መገለጫ የሆኑ የአንድነት፣ የአብሮነትና የአዎንታዊ መስተጋብር እሴቶች እንዲጎለብቱ ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች ማከናወን ይገባል።

"የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማህበራዊ መስተጋብሮቻችን ያለንን አንድነት በማጠናከር ለሀገር ብልጽግና መሥራት ይገባናል" ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለልና ለሕዝብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተጨማሪም በተቋማት የሚታዩ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ በዓሉ ያስገኘውን ትሩፋት ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም በበኩላቸው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት!'' በሚል ቃል በክልሉ በልማትና በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን  አስታውሰዋል።

ኅዳር 29 ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እውቅና የሰጠ ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ዕለት መሆኑን ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፤ በዓሉ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ያጠናከረና እርስ በእርስ ያስተሳሰረ ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ የህዝቦች የእኩልነት መብት በሕገ መንግሥት የተረጋገጠበት መሆኑን አስታውሰው፣ የክልሉ ሕዝብ  በጅግጅጋ ከተማ በሚከበረው በዓል ላይ የሚታደሙ እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናገድም አስገንዝበዋል።

በበዓሉ የተሳተፉት አቶ ቶፊቅ መሐመድና ወይዘሮ ነቢላ መሐመድ በበኩላቸው አብሮነትንና አንድነትን በማጠናከር በክልሉ የተጀመሩ የሰላምና የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የክልሉን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎችን በተሻለ ለመመለስና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራም ጠይቀዋል።

አገራዊ አንድነት የሰፈነባት የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር በሚያስችል መልኩ በዓሉን ማክበር እንደሚገባም ተናግረዋል። 

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም