የቻይና ኮንግረስ ፓርቲ አባላት ገላን የሚገኘውን ኤ ኤም ጂ ቡና ላኪ ድርጅትን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ) ፣- የቻይና ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገላን የሚገኘውን ኤ ኤም ጂ ቡና ላኪ ድርጅት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶና ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ተገኝተዋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ተወዳጅ ጣዕም ያላቸው ቡና በስፋት በማምረት ለተለያዩ አገራት በመላክ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የምትልከው ቡና በጥራትም ሆነ በማምረት አቅም እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከምትልክባቸው አገራት መካከል ቻይና ተጠቃሽ መሆኗን አስረድተው፤ የቻይና ባለሃብቶች በዘርፉ በስፋት ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።

በቻይና ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የግብርናና የገጠር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዱ ጂሃኦ በበኩላቸው በቻይና ገበያ የኢትዮጵያ ቡና እየታወቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከጉብኝቱም የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በቡና ዘርፍ በስፋት መሰማራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የቻይና ባለሀብቶች በቡና ማቀነባበሪያ ዘርፍ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም