በሥራ ላይ የቆየውን የሙስና መከላከል ስትራቴጂ በመከለስ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦ በሥራ ላይ የቆየውን የሙስና መከላከል ስትራቴጂ በመከለስ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

"ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በኅብረት እንታገል" በሚል መሪ ኃሳብ 20ኛው አገር አቀፍ የፍትህ ተቋማት የፀረ-ሙስና ቀን የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ጊዜ፤ ሙስና አገርን እድገት በመፈተን የፍትሕ ተቋማትን ተዓማኒነት አደጋ ላይ የሚጥል የሥነ-ምግባር ጉድለት ነው ብለዋል። 

ፍርድ ቤቶች ፍትሕ ሰጪ ተቋማት በመሆናቸው በዳኝነት ሂደት ሕዝብና መንግሥት የጣለባቸውን አደራ በፍጹም ታማኝነት በመወጣት ለሙስና ትግሉ አዎንታዊ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የፍትሕ ተቋማት በሙስና ወንጀል ተጋላጭነት የሚፈተኑ በመሆናቸው ጫናውን በመቋቋም አገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት በማገልገል ተጠያቂነት የማስፈን አገራዊ አደራ እንዳለባቸው አስገንዝዋል።

የሙስና ወንጀል በፍትሕ ተቋማት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ከሆነ የፍርድ ቤቶችን ተዓማኒነት በማጉደል ዜጎች በፍትሕ ተቋማቱ ላይ እምነት እንዲያጡ ያደርጋል ብለዋል።


 

ሙስናን መከላከል ካልተቻለ እድገትና ኢንቨስትመንት እንዲገታ በማድረግ ውጤታማነትና ፈጠራን በማዳከም በአገርን ህልውና ውስጥ እንደሚከት ገልጸዋል።

በዚሁ መነሻነትም ፍርድ ቤቶች የሙስና ተጋላጭነትን በመቀነስና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። 

ለዚህም በሥራ ላይ የቆየውን የሙስና መከላከል ስትራቴጂ በመከለስ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የክለሳ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው፤ ሙስናን ለመከላከል የሃብት ምዝገባ፣ የተጋላጭነት ጥናት፣ የሥነ-ምግባር ግንባታና ግንዛቤ ፈጠራ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የፍትሕ ተቋማት የሙስና ተጋላጭነት አመላካች የጥናት ውጤት መካሄዱን ጠቅሰው፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጋላጭነት ጥናት ውጤቱን ተግባራዊ ለማድረግ የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።

የመሬት ዘርፍ፣ የካሳ ክፍያ፣ የመንግስት ግዥ፣ ሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ የመንግስት አገልግሎት ግንባር ቀደም የሙስና ተጋላጭ ዘርፎች መሆናቸው አመላክተዋል። 

የሙስና ወንጀል ለመከላከል ከፍትሕና ተጋላጭነት ከሚስተዋልባቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተጠያቂነት እንዲሰፍን እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመድረኩም አገራዊ የሙስና ተጋላጭነትን ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮን የሚያመላክቱና የፍትሕ ተቋማት የሙስና ተጋላጭነትን የሚያሳዩ የመነሻ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም