በአማራ ክልል ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍና የማበረታታት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ጎንደር፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍና የማበረታታት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዶክተር አህመዲን መሃመድ ገለጹ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አህመዲን መሃመድ በጎንደር ከተማ የሚገኘውን አባይ ጋርመንት ፋብሪካ የምርት እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡

ዶክተር አህመዲን በዚሁ ጊዜ በክልል ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍና በማበረታታት በኩል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጨርቃ ጨርቃና አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጪ የሚገቡ የአልባሳት ምርቶችን በማስቀረት ሰፊ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ የግብዓት አቅርቦትና የገበያ ትስስር በመፍጠር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል፡፡

''የአባይ ጋርመንት ፋብሪካም ከውጪ የሚገቡ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ሰፊ አቅም እንዳለው መገንዘብ ችለናል'' ብለዋል  ዶክተር አህመዲን፡፡


 

ፋብሪካው በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተደራጀና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ጥራትና ተወዳዳሪነት ያላቸው አልባሳትን የማምረት አቅም አሟጦ እንዲጠቀም ድጋፍ ይደረጋልም ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው፤ የፋብሪካው በአካባቢው መቋቋም ለስራ አጥ ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለአምራች ኢንዱስ ትሪዎች መጠናከርና መበራከት ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ የተለያዩ የማበረታቻ ስርዓቶችን በመዘርጋት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ ማናየሽ ተሰማ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው ጂንስ ሱሪዎችንና ቲሸርቶችን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ነው፡፡

ፋብሪካው ባለፈው ዓመት ለሀገር ውስጥ ገበያ ካቀረበው የአልባሳት ምርት ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ማዳኑን ጠቁመው፤ ዘንድሮም በተመሳሳይ ዕቅዱን ለማሳካት በምርት ስራ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በመጠቀም በተለያዩ ዲዛይኖችና የጥራት ደረጃዎች ልዩ ልዩ የአልባሳት ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት 800 ለሚደርሱ ሰራተኞች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፤ በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲሸጋገር ለ3 ሺህ ያህል ሰራተኞች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የሚገኘው በአባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር የአባይ ጋርመንት ፋብሪካ በ2012 ዓ.ም በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ በክልሉ መንግስትና በባለሃብቶች ትብብር የተቋቋመ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም