የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነድ እያዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2016 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነድ እያዘጋጀ ነው። 

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ያዘጋጀውን ረቂቅ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነድ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። 

 ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚሰሩ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቷል።

ይህም ወቅታዊ፣ ግልጽና ቀልጣፋ መረጃዎችን የመለዋወጫ ምህዳር ለማስፋት ያስችላል ነው ያሉት።

የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዱ በተለይም ኮሚሽኑ ለተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላቶች የሚያስተላልፋቸውን መረጃዎች በምን መልኩና ለማን ምን አይነት መረጃ መቅረብ አለበት የሚለውን ለማመላከት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በቀጣይ ኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዱን ከዘርፉ ተዋናዮች የሚሰጡት ገንቢ ሃሳቦች በማዳበር  ሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሻንቆ ደለለኝ በበኩላቸው የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዱ  የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሰፊ እድል እንዳለው ገልጸዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ትልቅ ሃብትን የሚጠይቅ በመሆኑ አጋር አካላቶች በዚህ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዱ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም